ባለፉት 5 ወራት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 3 ኩንታል የሚጠጋ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ቀርቧል - ቢሮው

104

አሶሳ፤ ህዳር 30/2015(ኢዜአ) ባለፉት አምስት ወራት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሶስት ኩንታል የሚጠጋ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን የክልሉ ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ  30 ኩንታል ወርቅ ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ሃላፊ አቶ ናስር መሃመድ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፉት አምስት ወራት በማህበር በተደራጁ ወርቅ አምራቾች የተመረተ ሶስት ኩንታል የሚጠጋ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መቅረቡን አስታውቀዋል።

ምርቱ ከእቅዱ ሲነጻጸር ግን ዝቅተኛ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው በጥቁር ገበያ የወርቅ ምርቱ በጠረፍ በኩል ከሃገር እንዲወጣ የሚደረገው ህገ ወጥ ተግባር ለአቅርቦቱ ዝቅተኛ መሆን ምክንያት ነው ብለዋል።

ችግሩን ለማስቀረት ከወረዳ እስከ ፌደራል የተቀናጀ ጠንካራ ግብረሃይል ተደራጅቶ   ቁጥጥርና የመከላከል እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስረድተዋል።

በቅርቡ በድንበርና  በአሶሳ አውሮፕላን ማረፊያ  በኩል ሊወጣ የነበረ 400 ግራም ወርቅ በቁጥጥር ስር መዋሉን አቶ ናስር ጠቅሰዋል።

30 ህገወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎችን ፈቃዳቸውን በመሰረዝ በድርጊት የተሳተፉ 29 ግለሰቦች በፍርድ ቤት ክስ ለመመስረት ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ህገወጥ ዝውውርን ከመከላከል ባሻገር ምርታማነትን ለማሳደግ  በማህበር ለተደራጁ አምራቾች 13 የወርቅ ድንጋይ መፍጫ ማሽኖች ማቅረቡንና በምርት ወቅት በተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት በቴክኖሎጂ የመደገፍ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

በውላቸው መሠረት ያልሠሩ የወርቅ ኩባንያዎች ፈቃዳቸውን ከመሰረዝ ጀምሮ አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አቶ ናስር  አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአሶሳ ቅርንጫፍ ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ ስዩም ገብሬ፤ ብሔራዊ ባንክ ህጋዊ ወርቅ ግብይትን ለማበረታታት 50 ግራም ወርቅና ከዚያ በላይ ለሚያመጡ  አምራቾችና አቅራቢዎች   የሚሰጠው የ35 በመቶ ተጨማሪ ክፍያ በቅርንጫፉ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ብለዋል።

አምራቾችና አቅራቢዎች  የወርቅ ሃብቱን በሚሰበስቡበት አካባቢ በቂ ቅርንጫፍ ባለመኖሩ ባስገቡት ወርቅ ልክ ጥሬ ገንዘብ እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ  መሆኑን አስረድተዋል።

ባንኩ ወርቅ በስፋት በሚመረትባቸው የክልሉ ወረዳዎች ተጨማሪ ቅርንጫፎችን ለማስፋፋት ጥረት እንደሚያደርግ አቶ ስዩም ጠቁመዋል።

በአሶሳ ዞን በባህላዊ መንገድ የተመረተውን ወርቅ ወደ ባንክ ሲያስገቡ ኢዜአ ያነጋገራቸው አቶ አሳዲቅ አልመሃዲ በሰጡት አስተያየት፤ የህገወጥ ወርቅ አዘዋዋሪዎች ድርጊት ሀገርን ይጎዳል ሲሉ ገልጸው የጥቁር ገበያ የወርቅ ግብይትን ለማስቀረት ህግን በማክበርና በማስከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  ፈቃድ አውጥተው ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚያስገቡ  120 ወርቅ አቅራቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፤ በክልሉ ከሚገኙ 21 ወረዳዎች በአብዛኛዎቹ  የወርቅ ሃብት እንደሚገኝ በዳሰሳ ጥናት መረጋገጡን የማዕድን ሃብት ልማት ቢሮው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም