በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ ምርትና ምርታማነት አንዲጎለብት አስችሏል - የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ

204

ሐረር (ኢዜአ) ህዳር 30/2015 በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ሶስት ዓመታት የተከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ የአካባቢን አየር እርጥበት በመቀየር ምርትና ምርታማነት አንዲጎለብት ማስቻሉን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ ።

የመስኩ የስራ ሃላፊዎች በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሀረማያ ወረዳ የተከናወነ ያለውን የተፋሰስ ልማት ሰራዎችን ጎብኝተዋል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ  በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአካባቢ ጥበቃና በተፋሰስ ልማት የተከናወኑ ስራዎች አመርቂ ውጤት በማሳየት ላይ ናቸው።

በተፋሰስ ልማቱ በተከናወኑት ስራዎችም የተራቆቱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

እንዲሁም ከዚህ ቀደም ውሃ ያልነበረባቸው መሬቶች የከርሰ ምድር ውሃ ማመንጨት መጀመራቸው በተለይ በመስኖ ለሚከናወነው የስንዴና ሌሎች  የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች ከፍተኛ አስተዋጽዎ ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ማረጋገጥ እየቻለ መሆኑን ነው አቶ ጌቱ የተናገሩት።

እንደ አቶ ጌቱ ገለጻ በክልሉ በሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የእርሻ መሬት ሰፋት መጨመሩንና የደን ሽፋንም በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ በተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ላይ ከ4 ነጥብ 4 ቢሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን የጠቀሱት አቶ ጌቱ፤ በዚህም ጥሩ የጽድቀት መጠን እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘንድሮው የበጋ ስራ በ6 ሺህ 448 ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎች እንደሚከናወኑና  በክረምቱ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን የተለያዩ ችግኞች  እንደሚተከሉ ተናግረዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌታሁን ንጋቱ በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና ልማት ስራዎች ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት አድርጓል።

በተለይ የተፋሰስ ልማት ስራው በዞኑ ለ13 ዓመታት ጠፍቶ የነበረው የሃረማያ ሐይቅ እንዲመለስ ማስቻሉን ነው አቶ ጌታሁን የገለጹት።

በዘንድሮ በጋ ወራትም በዞኑ በ510 ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚከናወን ገልጸው በዚህም ከ800ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። 

በደን መጨፍጨፍ ምክንያት አካባቢያችን ምድረ በዳ ሆኖ ለዓመታት ቆይቷል የሚሉት የሐረማያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብዲ አልይ፤ ባለፉት ዓመታት ባከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ አካባቢው ወደ ለምለምነት መቀየሩን ገልጸዋል።

በተለይ በአሁኑ ወቅት በተፋሰሶቹ ላይ ጠፍተው የነበሩ ምንጮች መጎልበታቸውንና የከርሰ ምድር ውሃ በቅርበት ማግኘት በመቻላቸው ምርትና ምርታማነትን እያሳደጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የአካባቢው የአየር ንብረት ወደ ነፋሻነት መለወጡን የተናገሩት አቶ አብዲ በቀጣይም ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የተፋሰስ ልማት ስራ አጠናክረን በመስራታችን ለዘመናት አጥተነው የነበረውን አረንጓዴ እፅዋትና ነፋሻማ አየር መመለስ ችለናል" ያሉት ደግሞ የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ኢብሳ አብዱላሂ ናቸው።

በተለይ በአካባቢው ጠፍቶ የነበረው የከርሰ ምድር ውሃና የሃረማያ ሐይቅ በተፋሰስ ልማት ስራ መመለስ ችለናል፤ ይህንንም በቀጣይም አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም