ፖሊስ ከ26 ሺህ ዶላር በላይ ሲያዘዋውር የነበረን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አዋለ

137

አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 30/2015 የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምርያ በሕገ ወጥ መንገድ 26 ሺህ 400 የአሜሪካ ዶላር ሲያዘዋውር ደርሼበታለሁ ያለውን ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ ዋና ሳጅን ጀማል አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቡ ትናንት ምሽት ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።

ግለሰቡ ከአዲስ አበባ ወደ ጅግጅጋ ከተማ ኮድ 3 ኦሮ የሰሌዳ ቁጥር 74663 በተለምዶ 'ዶሊፊን' ተብሎ በሚጠራው አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ውስጥ ስውር ቦታ የውጭ ሀገር ገንዘቡን ደብቆ በመጓዝ ላይ እንዳለ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ በቁጥጥር መዋሉን አስረድተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ግለሰቡ በሕገ ወጥ መንገድ ሊያዘዋውር ከያዘው የውጭ ሀገር ገንዘብ ጋር በቁጥጥር ስር የዋለው በአዲስ-አዳማ የፍጥነት መንገድ ተቆጣጣሪ ፖሊሶች ነው።

ዋና ሳጅን ጀማል አክለውም ግለሰቡ ከነ ገንዘቡ በቁጥጥር ስር የዋለው ቱሉ ዲምቱ የፍጥነት መግቢያ ኬላን አልፎ ለማምለጥ ሲሞክር እንደሆነ ጠቅሰው፤ በፖሊስ ምርምራ እየተደረገበት መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም