በክልሉ የእርሻ ቴክኖሎጂ አቅርቦት በትኩረት እየተሰራ ነው - ግብርና ቢሮ

127

ባህርዳር (ኢዜአ) ህዳር 30/2015 በአማራ ክልል የእርሻ ቴክኖሎጂ አቅርቦትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በአምባሰል የንግድ ስራዎች ድርጅት በኩል ከውጭ ያስገባቸውን ከ100 በላይ ዘመናዊ የእርሻ ማሽነሪዎችና ቴክኖሎጂዎችን ተረክቧል።

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ሃይለማርያም ከፍያለው በርክክቡ ወቅት እንዳሉት በምግብ ራስን ለመቻልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ማነቆ የሆኑ የእርሻ መሳሪያዎችና የምርጥ ዘር እጥረትን ለመፍታት እየተሰራ ነው።

ክልሉ በእርሻ ከሚለማው 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ አብዛኛው የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ለማምረት ተስማሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና እስካሁን ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እየለማ ያለው መሬት በጣም አነስተኛ ነው ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታትም በዚህ ዓመት ብቻ ከ1 ሺህ በላይ ትራክተሮችንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን በተደረገ ጥረትም 316 የእርሻ ትራክተሮችንና ሌሎች ማሽነሪዎችን በመረከብ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ ተችሏል ብለዋል።

ለ2ኛ ጊዜ በተደረገው ርክክብም ትራክተሮችን፣  የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮችንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን መረከብ መቻሉን ሃላፊው ገልፀዋል።

የክልሉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የግብርና ዘርፉን በቴክኖሎጂ የማዘመን እንቅስቃሴም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል።

የአምባሰል ንግድ ስራዎች ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሃሰን የሱፍ በበኩላቸው አምባሰል በ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰረታዊ ሸቀጦችን ከውጭና ከአገር ውስጥ ፋብሪካዎች እየተረከበ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በተጨማሪም የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ ማዳበሪያ፣ ጸረ ተባይ ኬሚካል፣ ማጭድና ሌሎች የእርሻ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአሁኑም 37 ትራክተሮችን ጨምሮ ከ100 በላይ የእርሻ ማሽነሪዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በማስገባት ለግብርና ቢሮ ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይ አንድ ወር ጊዜ ውስጥም በመጋዘን ውስጥ፣ በወረታ ደረቅ ወደብና ከጅቡቲ ወደብ የሚጓጓዙ 63 ትራክተሮችንና ከ8 ሺህ 700 በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን የማስረከብ ስራ ይከናወናል ብለዋል።

በቀጣይ ለሚቀርቡት  የሜካናይዜሽን እርሻ ቴክኖሎጂዎች አርሶ አደሩ ቀድሞ በመቆጠብና ከአበዳሪ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመመስረት የሚመጡትን በመውሰድ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም