የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማምጣት በትኩረት እንዲሰራ ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ

170

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማምጣት በትኩረት እንዲሰራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የ2015 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ገምግሟል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፤ የበጀት ዓመቱን የሦስት ወራት አፈጻጸም ባቀረቡበት ወቅት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረው የገንዘብ መጠን እንዳይጨምር በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የዋጋ ንረቱ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር ሲታይ መጠነኛ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቁመው፤ ለዚህም በግብርናው ዘርፍ የተሰሩ ሥራዎች የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ከወጪ ንግድ አንጻር 977 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ገልጸው፤ የአበባና ቡና ምርት ከፍተኛ አፈጻጸም እንዳስመዘገቡና በአንጻሩ የወርቅ፣ የጨርቃጨርቅና የቆዳ ምርቶች ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳላቸው አመላክተዋል።

የገቢ ምርቶችን በተመለከተ ከ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር በላይ የገቢ እቃዎች መግባታቸውን ገልጸው፤ ይህም የወጪና ገቢ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለው ያመላከተ ነው ብለዋል።

የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በጥንካሬ የሚታዩና አሁንም ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል።

በገቢና ወጪ ንግድ መካከል ያለውን የንግድ ሚዛን ከዚህ የበለጠ እንዳይሰፋ በትኩረት መሥራት እንዲሁም የገንዘብና የፊስካል ፖሊሲዎች በጥብቅ ሊተገበሩ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል።

ከጥቁር ገበያ ጋር በተያያዘ እየታዩ የሚገኙ ሕገ-ወጥነቶች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት ረገድ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ባንኮች ጤናማና ትርፋማ ሆነው እያሳለፉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የባንኮች አሁን ያላቸው የተቀማጭ መጠን 1 ነጥብ 8 ትሪሊየን መድረሱን ጠቅሰው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባውን የገንዘብ መጠን የመቆጣጠር ሥራ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፋይናንስ ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ የዲጂታል ባንኪንግ ሥርዓት እየተስፋፋ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጥቁር ገበያን ለመከላከል በተወሰደ እርምጃ እስካሁን ከ400 በላይ ግለሰቦች ተይዘው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑን አንስተዋል።

በብድር አመላለስ የነበሩ ችግሮች መሻሻላቸውንና ከወርቅ ገበያ መቀዛቀዝ ጋር የተያያዘው ጉዳይም በተለያዩ አካባቢዎች ካለው የጸጥታ ችግር አንፃር መሆኑን አስረድተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፤ ባንኩ ይህንን የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማምጣት በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በወጪ እና ገቢ ንግድ ሚዛን መዛነፍ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል እና የንግድ ሚዛኑን ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት።

በጥቁር ገበያ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እና የተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት እንዲኖር የማድረግ ሥራውን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አመላክተዋል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚገኙ የውጭ ምንዛሪዎችም ለታለመላቸው ዓለማ እየዋሉ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም