የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነትና አብሮነት በዘላቂነት ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን - ወጣቶች

153

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 29 ቀን 2015 የኢትዮጵያን ሰላም፣ አንድነትና አብሮነት በዘላቂነት ለማስቀጠል የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በሐዋሳ ከተማ በተከበረው 17ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ የታደሙ ወጣቶች ገለጹ፡፡

የአካባቢያችንን ሠላም በመጠበቅ እንደ ሀገር የተጀመረው ሁለንተናዊ ጥረት ዘላቂ እንዲሆን የሚሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

17ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በሐዋሳ ስታዲየም ሲከበር የታደሙ የተለያዩ ወጣቶችን ኢዜአ አነጋግሯል።

በበዓሉ ላይ የታደመው ወጣት አቡበከር አብዱልፈታ፤ አብሮነታችንና ወንድማማችነታችን ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ሲል ገልጿል።

የአገር ሰላም ማጣት ዜጎችን ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት ጠቅሶ፤ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።

በተለይ ወጣቱ ለሰላም መስፈን የድርሻውን በንቃት መወጣት እንዳለበት አመልክቶ፤ የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንወጣለን ብሏል።

በወለኔ  “ይሮት”  የተሰኘ የሽምግልናና የዕርቀ ሰላም ባህላዊ እሴት እንዳለ የተናገረው ወጣት አቡበከር፤ ባህላዊ የዕርቀ ሠላም እሴቶቻችንን በመጠበቅ የሀገራችንን ሠላም እናረጋግጣለንም ሲል ገልጿል።

አባቶቻችን ሠላሟንና አንድነቷን ጠብቀው ያቆዩልንን ሀገር መጠበቅና በፍቅር መኖር አለብን ያለው የጅማ ወጣት እስማኤል አባሜጫ በበኩሉ፤ አገራዊ አንድነትን በማስጠበቅ አገራዊ እምቅ ሀብታችንን መጠቀም አለብን ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ሀብት ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎችም እንደሚተርፍ ገልጾ፤ ኢትዮጵያውያን ያለንን ሀብት በፍቅር ብንጠቀምበት ለሌሎች መትረፍ እንችላለን ሲል ተናግሯል።

ጅማ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በፍቅር የሚኖሩባት ናት ያለው ወጣት እስማኤል፤ ይህንን እሴት በማጠናከር የአካባቢው ሠላም ፀንቶ እንዲቆይ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ ነው የገለፀው፡፡

የሠላም አምባሳደር በመሆን የአካባቢውን ሠላም በመጠበቅና በህዝቦች መካከል ወንድማማችነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሰራ እንደሚገኝ የተናገረው ደግሞ ወጣት ተመስገን ያዕቆብ ነው፡፡

የሲዳማ ክልል አስተዳደር አካላት በክልሉ አስተማማኝ ሠላም ለማስፈን እየጣሩ እንደሚገኙ ጠቅሶ፤ እኛም ከጎናቸው ሆነን ሠላማችንን ለማስጠበቅ እየሰራን ነው ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም