ልማት ባንክ በተያዘው በጀት ዓመት የአንድ ቢሊዮን ብር ቦንድ ለመሸጥ አቅዷል

90
አዲስ አበባ መስከረም 18/2011 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተያዘው በጀት ዓመት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ አንድ ቢሊዮን ብር የቦንድ ሽያጭ ለማከናወን አቅዷል። የባንኩ የእስትራቴጂ፣ ለውጥና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ሃይለየሱስ ለኢዜአ እንደተናገሩት እቅዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተዘጋጀ  ነው። ሽያጩ በባንኩ ዋናው መስሪያ ቤትና ቅርንጫፎች፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በተለያዩ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሚከናወን ይሆናል። እቅዱን በተሻለ መልኩ ለማከናወንም ሁሉም በጋራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል። የታላቁ የህዳሴ ግድብ በቦንድ ሽያጭ፣ በጉልበት እንዲሁም በተለያዩ ድጋፎች በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የሚገነባ ፕሮጀክት ነው። በመሆኑም ህብረተሰቡ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅ የጀመረውን አስተዋጽኦ ቦንድ በመግዛትና በተለያዩ ድጋፎች እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። ህብረተሰቡ ቦንድ በመግዛት ለወዳጅ ዘመድ ስጦታና ለተለያዩ ዝግጅቶች ማበርከት እንደሚችልም ተገልጿል። ባንኩ ባለፉት አምስት ዓመታት ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል በሰራው የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ በተጓዳኝ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የቦንድ ሽያጭ አከናውኗል። ለግድቡ ግንባታ ከህብረተሰቡ 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ሲሆን እስካሁን ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት መረጃ ያሳያል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ2003 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ግንባታውም ከ64 በመቶ በላይ መድረሱን መረጃዎች ያሳያሉ። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ በህብረተሰቡ ዘንድ የጀመርነውን እንጨርሰዋለን የሚል ቁጭት ተቀስቅሶ ነበር።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም