ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ድርጅት የወቅቱ ፕሬዝዳንትን ተቀብለው አነጋገሩ

436

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015  ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ድርጅት የወቅቱ ፕሬዝዳንት የሆኑትን የናሚቢያ ቀዳማዊት እመቤት ሞኒካ ጊንጎስ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

ውይይታቸው በአፍሪካ የሴቶችን አመራርነት ሚና ማጎልበትና የሴት መሪዎችን ብዛት ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ እና ቀዳማዊት እመቤት ሞኒካ ጊንጎስ በውይይታቸው በአፍሪካ የሴቶችን የመሪነት አቅም መጠቀምና የመሪዎችን ቁጥር ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረዋል።

የሴቶችን የሙያ፣ የክህሎትና የመሪነት ሚና ለማጠናከር በጋራ መሥራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የአፍሪካ ሴት መሪዎች ጥምረትን ጨምሮ በአህጉሪቷ ያሉ የሴት አደረጃጀቶች ጋር በጋራ እንደሚሰሩም እንዲሁ።

የሴት አመራሮችን ወደ ፊት በማምጣት ረገድ የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሌሎች አገሮች ጥሩ ምሳሌ መሆኑም ተነስቷል።

የናምቢያ ገዥ ፓርቲ በቀጣይ በአገሪቷ ለሚደረገው ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ ሴት ዕጩ እንዳቀረበ ተገልጿል።

ቀዳማዊት እመቤት ሞኒካ ጊንጎስ ከቀዳማዊ እመቤትነታቸው ባሻገር በሕግ ባለሙያነታቸው፣ በሥራ ፈጣሪነታቸው እና በድርጅት አመራርነት ብቃታቸው የሚጠቀሱ ሴት ናቸው።

የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2002 ‘የአፍሪካ ቀዳማይ እመቤቶች ፀረ-ኤች አይ ቪ/ኤድስ ድርጅት’ በሚል ስያሜ የተቋቋመ ቢሆንም አህጉራዊ ተልዕኮውን በማስፋት የወቅቱን ስያሜ ይዟል።