የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ከሶማሊያ አቻቸው ጋር ተወያዩ

287

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ በሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከድር መሃመድ ኑር የተመራውን የልዑካን ቡድን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

ሚኒስትሩ ከሶማሊያ አቻቸው ጋር በሁለትዮሽ የሰላምና የደህንነት ጉዳዮች እንዲሁም በቀጠናው የፀጥታ ሁኔታ ምክክር አድርገዋል።

በምክክራቸው ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ሰላምና ደህንነት ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል ዶክተር አብርሃም አስታውቀዋል።

የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልከድር መሃመድ ኑር በበኩላቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለሶማሊያ ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል እያደረገው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችልም እምነታቸውን መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም