የሰላም ሚኒስቴር በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ያደሳቸውን 23 የአቅመ ደካማ ቤቶች አስረከበ

312

ባሌ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 የሰላም ሚኒስቴር በባሌ ዞን ጎባ ከተማ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ያደሳቸውን 23 የአቅመ ደካማ ቤቶች አስረከበ።

በመርሓ ግብሩ ላይ በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሂሩት ደሌቦ እንዳሉት ሚኒስቴሩ ሰላምን የሚያረጋግጡና የህዝቦች አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየሰራ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባር በተጨማሪ በተለያየ መልኩ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን እያከነወነ መሆኑንም ገልጸዋል።

በባሌ ዞን ጎባ ከተማ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ታድሰው ለተጠቃሚዎች የተላለፉት 23 ቤቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።

ለቤቶቹ እድሳት ስራ ከ4 ሚሊዬን ብር የሚበልጥ ወጪ መደረጉን ገልጸው የአካባቢው ሕብረተሰብም የቤት እድሳቱን በጉልበት ማገዙን ተናግረዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አድሶ ካስረከባቸው ቤቶች በተጓዳኝ ለአካል ጉዳቶኞችና አቅመ ደካሞች የአካል መደገፊያና አልባሳትንም ድጋፍ አድርጓል ነው ያሉት።

የጎባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሽመልስ አለሙ በበኩላቸው የሰላም ሚኒስቴር ላደረገው በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ህዝብን በማሳተፍ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች መስራት እንደሚቻል ልምድ የወሰዱበት እንደሆነም ተናግረዋል።

የቤት እድሣት ከተደረገላቸው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ወይንሸት ታደሰ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት ከነልጆቻቸው ሊፈርስ በተቃረበ ደሳሳ ጎጆ ውስጥ ሲቸገሩ መቆየታቸውን አስታውሷል።

የሰላም ሚኒስቴር ከጎባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ባደረጉላቸው ድጋፍ ከነበረባቸው ችግር በመገላገላቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ሌላዋ ቤታቸው የታደሰላቸው ወይዘሮ መሰረት ከበደ በበኩላቸው ከነበሩበት አስቸጋሪ ህይወት እፎይታ ማግኘታቸውን ገልጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም