ሕዝበ-ሙስሊሙ በመንግሥት የተጀመረውን ሙስና የመከላከል ጥረት በሚችለው አቅም ሁሉ እንዲያግዝ ጥሪ ቀረበ

155

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 29/2015 መንግሥት እያካሄደ ያለውን ሙስናን የመከላከል ጥረት ሕዝበ-ሙስሊሙ በተቻለው አቅም እንዲያግዝ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ። 

በነገው የጁምዓ ሰላት የሙስናን ወንጀል አስከፊነት በሚመለከት በየመስጂዶች ትምህርት (ሁጥባ) የሚሰጥ መሆኑም ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼኸ ሱልጣን ሐጅ አማን ጉዳዩን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

ሼኸ ሱልጣን በማብራሪያቸው በእስልምና አስተምህሮት ሙስና ለሰጪውም ይሁን ለተቀባዩ ከፍተኛ ወንጀልና በፈጣሪ (በአላህ) ዘንድ የሚያስጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።

በሙስና የሚገኝ ማንኛውም ንብረትም ሆነ ሀብት በረከት የሌለው፣ ደስታን የማይሰጥና በፈጣሪም በእጅጉ የተጠላ መሆኑን ገልጸው በእምነታችን ዘንድ የተጠላ (ሃራም) የሆነውንና የሚያስጠይቀንን ወንጀል በመዋጋት ለእውነትና ለመልካም ተግባር በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

በመንግሥትም እየተካሄደ ያለውን ሙስናን የመከላከል ጥረት ሕዝበ-ሙስሊሙ በቻለው አቅም ሁሉ ሊያግዝ ይገባል ነው ያሉት።

የሙስና እና የሌብነት ተግባር በመልካም ስብዕና ለምንገነባው ትውልድ ፈተና እና ለሀገር ውድቀት መንስኤ መሆኑን በማስረዳት።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ሼኸ ሁሴን በሽር በበኩላቸው፤ በመንግሥት የተጀመረውን ሙስናን የመከላከል ጥረት ለማገዝ በምክር ቤቱ በኩል ዝግጅት ተደርጎ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

ከሙስና መከላከል ሥራዎች መካከል አንዱ በማስተማር መልካም ስብዕና ያለው ዜጋ ማፍራት በመሆኑ በየመስጂዶችና ሌሎች አጋጣሚዎችም ሕዝበ-ሙስሊሙን የወንጀሉን አስከፊነት የማስተማር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም በነገው ዓርብ የጁምዓ ሰላት በአዲስ አበባ  በሁሉም መስጂዶች ኢማሞች በጉዳዩ ዙሪያ ትምህርት (ሁጥባ) ያደርጋሉ ብለዋል።

በቀጣይም ለመስጂድ ኢማሞችና ለዲን ትምህርት ቤት (መድረሳ) አስተማሪዎች ሥልጠናዎች ይሰጣሉ በማለት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም