የደቡብ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታወቀ

274

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 የደቡብ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚቴ ማቋቋሙን ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንደገለጹት የልማትና ዕድገት ጸር የሆነውን ሙስናን ለመከላከል በቁርጠኝነት ይሰራል።

በክልሉ ሙስናና ብልሹ አሠራርን መታገል የሚያስችል አምስት አባላት ያሉት የፀረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙንም ነው የገለጹት።

በዚሁ መሰረት አቶ አለማየሁ ባውዲ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚቴውን በሰብሳቢነት የሚመሩት መሆኑን አመልክተዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሶፎኒያስ ደስታ፣ የክልሉ ስነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበራ ኪጴ፣ የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ፈዲላ አደምና በርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት የመልካም አስተዳደርና የአካባቢ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑሪዬ ሱሌ ደግሞ አባል ሆነው መሰየማቸውን አስታውቀዋል።

በየደረጃው የሚፈጸመውን ሙስናና ብልሹ አሰራር በመታገል ረገድ የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ጥቆማ መቀበል የሚያስችሉ የስልክ አድራሻዎች ይፋ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

በክልሉ በሁለም የአስተዳደር እርከኖች የጸረ-ሙስና ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቁት ርዕሰ መስተዳድሩ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

በክልሉ የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት ስራቸውን በላቀ ቁርጠኝነትና በውጤታማነት እንዲያከናውኑ ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደረግም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም