በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት ዛሬ የተከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በሰላም ተጠናቋል- የሰላምና ጸጥታ ቢሮ

319

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት ዛሬ የተከበረው 17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የክልልና የፌዴራል የጸጥታ መዋቅር ከአካባቢው ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈና የተቀናጀ ጠንካራ የጸጥታ ስራ ሲያከናውን መቆየቱን የቢሮው ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጥሞቲዮስ በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚህም የበዓሉ ሂደት ያለምንም የጸጥታ ችግር በታሰበው ልክ በተሳካ ሁኔታ ተከብሮ መጠናቀቁን አስታወቀዋል።

በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ የጸጥታ አካላትና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ምስጋና አቅርበዋል።

በዓሉን ለማክበር ከመላው የሀገሪቱ ክፍል የመጡ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተወካዮች እስኪመለሱ ድረስ በተለመደው መልካም መስተንግዶ በማቆየት ለመሸኘት ዝግጅት መደረጉም ተመልክቷል።

በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት ዛሬ በሀዋሳ በድምቀት በተከበረው 17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የፌደራልና የክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ታድመዋል።