ህግን የማስከበር ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ

101

በመላው የፀጥታ ሐይላችን የህይወት መስዋዕትነት እና በህዝባችን ቀና ተባባሪነት እየሰከነ የመጣው ሰላማችንን ወደ ኋላ ለመመለስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ለመቆጣጠር የሚያከናውነውን ህግን የማስከበር ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ያወጣው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ይቀርባል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተማችን አዲስ አበባ ምንም አይነት የፀጥታ ሥጋት ሳይጋረጥባት ይልቁንም የልማትና የዕድገት ጉዞዋን ተጠናክሮ ከመቀጠሉም ባሻገር ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ሰርተው እንዲገቡ መላው የፀጥታ ኃይሉ የከፈለው መስዋትነትና ህዝባችን የነበረው የተባባሪነት መንፈስ ለተገኘው ሰላም መሰረት ነው።

ከለውጡ በኃላ ሃገራችን ያጋጠማትን የፀጥታ መደፍረስ ችግር እንደ ምቹ ሁኔታ የቆጠሩ የተለያዩ ፅንፈኛ ሐይሎች በተለይም የፅንፈኛው ሸኔና በተለያየ ስም የተደራጁ ፅንፈኛ ሃይሎች ከተማችንን የሽብር ቀጠና ለማድረግ አቅደው በመንቀሳቀስ ከተደራጀ ወንጀለኝነት ጀምሮ የአውዳሚነት አቅማቸው ከፍተኛ የሆኑ የጦር መሳሪያዎችን ጭምር ወደ ከተማችን ለመስገባት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከተማችን አዲስ አበባ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የስበት ማዕከል ከመሆኗ ባሻገር የሐገራችን ብሔር-ብሔረሰቦች በሰላም ፤በፍቅር እና በአብሮነት የሚኖሩባት ትንሿ አትዮጲያ ነች፡፡ እነዚህ ፅንፈኛ ሃይሎች የአዲስ አበባን ሰላምና ፀጥታ ማወክ የዕኩይ ተግባራቸው ዋና አጀንዳ የማድረጋቸው መነሻም ይህው ነው።

መንግስት በተከተለው የሰላም መስመር ሐገራችን ከነበረችበት የጦርነትና የሥጋት አውድ ለማላቀቅ በርካታ ተግባራት እየተከናወነ ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎን በሐገራችን ሆነ በከተማችን በአስከፊ ሁኔታ የተንሰራፋውን የሙስናና የሌብነት ተግባር መንግስት በፍፁም ቁርጠኝነት ለመዋጋት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በህዝብ ፍላጎትና በመንግስት ቁርጠኝነት የተጀመሩ የሰላምና የፀረ-ሌብነት ትግሉን ለማኮላሸት ሁሌም የማይተኙት እነዚህ ፅንፈኛ ሃይሎችና እና አንድ አንድ ግለሰቦች መልካቸውን ቀይረው መከሰታቸውን ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ የወንጀል ምርመራ መዝገቦችን ዋቢ አድረጎ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቋል።

በዚህም መሰረት በቅርቡ በከተማችን በሚገኙ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በአንድ በኩል የዜጎችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የመማር መብትና ማንነታቸውንና ባህላቸውን መግለፅን እንደ ጫናና በሃይል በሌሎች ላይ እንደተጫነ አድርጎ የመቀስቀስ በሌላ በኩል ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ እየሞተ ነው የህዝብ ባህልና ማንነት ተዋረደ የሚሉ እርስ በእርሱ የሚቃረን የግጭት ማቀጣጠያ አጀንዳ በመፍጠር እንዲሁም የወልቃይትና የአዲስ አበባ ጉዳይ አንድ ነው የሚል መፈክር ይዘው ከመውጣት ባሻገር የሐገሪቱን ሰንደቅ ዓላማና የኦሮሚያ ክልል ባንዲራና ከሰንደቁ ላይ ላይ በማውረድና መሬት ለመሬት በመጎተት ከፍተኛ ድፍረት የፈፀሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሰሞኑን በተወሰኑ አንደኛና ጥቂት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የጥፋት አጀንዳቸውን ከተቀበሉ አንዳንድ መምህራንና ተማሪዎች ጋር በመሆን በማደናገርና በማወናበድ ምንም የማያውቁ አብዛኛው ተማሪዎችን ከፊት በማሰለፍ ባስነሱት ረብሻ በትምህርት ቤቶቹ ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ተረጋግጧል።

ከዚህም በሻገር ፅንፈኛ በሆኑ ማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው በመጠቀም የፀጥታ ሐይሉ ህጋዊ ተግባሩን እንዳይወጣ ለማሸማቀቅ ታስቦ ከዚህ በፊት የተቀረፁ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምስሎችን እና እርምጃ ተወስዶ የታረመን ድርጊት አሁን እንደተፈፀመ በማስመሰልና በማሰረጨት ህብረተሰቡ ለአመፅና ብጥብጥ እንዲተባበር እያነሳሱ መሆናቸውን ፖሊስ በመረጃ ያረጋገጠ ሲሆን ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸውን ዘጠና ሰባት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ ገልዖል።

አያይዞም የፀጥታ ሐይሉ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በሐሠተኛ ሚዲያዎችና የሃሰት ዘገባዎች ሳይሸማቀቅ ከህዝብና ከመንግስት የተሰጠውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን እና ህግ የማስከበር ግዴታውን እንደሚወጣ አስታውቋል።

አዲስ አበባ የወትሮ ሠላሟና የነዋሪዎቿ በሰላም ወጥቶ መግባት የሚያንገበግባቸው ግለሰቦችንና ሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደቱን ለርካሽ የፖለቲካ አላማቸው ለማዋል እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሃይሎችን ፤ በመለየት ህግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው ፖሊስ ህብረተሰቡም ልጆቹን ከመምከር ባሻገር የሠላሙ ፀር የሆኑ ግለሰቦችንና ቡድኖችን አጋልጦ ለፀጥታ አካላት በመስጠት የዘወትር ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል።

የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትና መረጃዎችን ለመስጠት በአዲስ አበባ ፖሊስ የመረጃ ስልክ ቁጥሮች 011-1-11-01-11 እና በነፃ የስልክ መስመር 991 ላይ በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚቻል የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም