የሚገጥሙንን ፈተናዎች በድል ተሻግረን ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን የመገንባቱን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

91

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 የሚገጥሙንን ፈተናዎች በድል ተሻግረን ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን የመገንባቱን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሐዋሳ እየተከበረ በሚገኘው 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አከባበር ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡

በመልዕክታቸውም “ኢትዮጵያ የሁላችንም ቤት ናት፤ ለሁላችን የሚሆን አውድ መፍጠር ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነው ችግሮችን በጋራ መፍታት ይኖርባቸዋል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎችን አብሮነት ለመሸርሸር የሚካሄዱ ዋልታ ረገጥ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያ ለአፍታ እንኳ ሰላም እንዳትሆን  የግጭት አጀንዳ ተቀብለው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የገጠሙንን ፈተናዎች በድል ተሻግርን የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክረን እንቀጥላልን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፈተናዎች የማትቆም ጠንካራ ሀገር መሆኗንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው "ያጠፉትም ያለሙትም አልፈዋል፤ እኛ ግን መገፋፋትና መጠላለፉን ትተን ለነገ መልካም ነገርን ለማሻገር መስራት አለብን" ሲሉ  ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን ሀገር ለማወክ ለሚሰራጩ የግጭትና የጥላቻ አጀንዳዎች ጆሮ ባለመስጠት አብሮነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠላቶች አጀንዳ ሁልጊዜም ጥላቻና ግጭት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ የጀመርነውን የመደመርና የፍቅር ጉዞ በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት መስራት አለብን ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም