የእያንዳንዳችን ችግር ሊፈታ የሚችለው የኢትዮጵያ ችግር ሲፈታ ብቻ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

149

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 29/2015 የእያንዳንዳችን ችግር ሊፈታ የሚችለው የኢትዮጵያ ችግር ሲፈታ ብቻ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ17ኛው የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ላይ ባስተላለፉት መልዕክት መላው ዜጋ በአንድነት በመቆም የሁሉም መኖሪያ የሆነችውን ኢትዮጵያን ከነክብሯ ለማስቀጠልና ለማጽናት በአንድነት ሊቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የሁላችንም ቤት ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በጋራ ማደግ፣ መበልጸግና በሰላም የሚኖርበት ሁኔታ መፍጠር ካልተቻለ መኖር፣ መበልጸግና ወጥቶ መግባት እንደሚያስቸግር ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ችግር በፊት ቀድሞ የሚፈታ የሰፈር ችግር እንደሌለም አስገንዝበዋል።

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የሁሉም ታሪክ፣ ቅርስና እሴት የኢትዮጵያ ሀብትና ኩራት ሆኖ የሚታይበት መሆኑን ገልጸው፤ ሁላችንም ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ መሆናችንና በኢትዮጵያ ጥላ ስር ውበታችን ጎልቶ የሚታይ መሆኑን የምንማርበት ዕለት በመሆኑ የኢትዮጵያዊነት ቀን የኢትዮጵያውያን የመማሪያ ቀን ስለሆነ እንኳን ደስ ያላችሁ ሲሉ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሁሉም ብሔሮች፣ ዜጎች፣ ባህሎችና ታሪኮች እያንዳንዳቸው ሰበዝ ሆነው ሲደመሩ ታላቋን፣ ድንቋን፣ ውቧን ኢትዮጵያ የሚያሳዩ ስለሆነ በተናጠል ጎልተን ለመታየት ሳይሆን በጋራ ለማበብ ልባችን የቀናና አዕምሯችን የሚያስተውል እንዲሆን ላሳስባችሁ እወዳለሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያን በአንድነት በመቆም ከነክብሯ ለማስቀጠልና ማጽናት እንደሚገባ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማንነቶችን በአግባቡ የሚያስተናግድና የሚይዝ የፌዴራል ስርዓት እየገነባን ጠንካራዋን ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን መቀጠል ይገባል ብለዋል።

ልዩነት ለመዝራት ያልተገባ አጀንዳ ለሚያናፍሱ አካላት በሙሉ በአንድነት በመቆም ጽናታችንን ልናሳይ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን የያዝነው የአንድነት የፍቅርና የመደመር ዕሳቤ እንዲሁም የመስራትና ጀምሮ የመጨረስ አቅማችንን በማጠናከር በአጭር ጊዜ የሀገራችንን ብልጽግና ዕውን እናደርጋለን ብለዋል።

የኢትዮጵያን ከፍታ ለሚጠሉት ሁሉ ዕድገታችንና ልማታችንን በማጉላት ለማሳየት የሚያስችል ዕድል እንዳለ ገልጸው፤ ለዚህም ዜጎች ሊተጉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም