በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን ኢትዮጵያዊ ባህልን በተላበሰ መስተንግዶ ለመቀበል ዝግጅት አድርገናል – ሆቴሎች

285

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 27/2015— 17ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር ወደ ሐዋሳ ከተማ የሚመጡ እንግዶችን ኢትዮጵያዊ ባህልን በተላበሰ መስተንግዶ ለመቀበል ዝግጅት ማድረጋቸውን የሆቴል አገልግሎት ሰጪዎች ገለጹ፡፡

17ኛው የብሄር፣ብሄሰቦችና ህዝቦች ቀን በሲዳማ ክልል አዘጋጅነት በሐዋሳ ከተማ በመጪው ሃሙስ ይከበራል፡፡

በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ኢዜአ ባደረገው ምልከታ አረጋግጧል።

ዝግጅቱን በተመለከተ የሐዋሳ ሴንትራል ሆቴል ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ውብሸት አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሆቴሉ አልጋ የተያዘላቸው እንግዶች ከዛሬ ጀምሮ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እንግዶቹን ኢትዮጵያዊ እንግዳ የመቀበል ባህልን በተላበሰ መልኩ ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት ባህላዊ የቡና ስነ-ስርዓት ጀምሮ የተለያዩ መስተንግዶዎች እንደሚኖሩ ተናግረዋል።

ባህላዊ ምግቦችም ተዘጋጅተው እንደሚቀርቡ ጠቅሰው፤ የበዓሉ መከበር ለሆቴሎች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

እንግዶች በሚኖራቸው ቆይታ የሚደሰቱበት የሆቴልና የሌሎች አገልግሎቶች እንደሚኖሩ ጠቅሰው፤ የእንግዶችን ቆይታ ለማራዘም የሚያስችል መስተንግዶ እንደሚሰጡ አስረድተዋል።

ይህም በከተማዋ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት እንደሚፈጥር ተናግረው፤ በሆቴሉ የሚያርፉ እንግዶች እቤታቸው እንዳሉ እንዲሰማቸው ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በአገር ደረጃ የሚከበሩና በርካታ እንግዶች የሚታደሙባቸው በዓላት የንግዱን ዘርፍ ከማነቃቃት ባለፈ የከተሞች ገጽታ ለመገንባት ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

የኬርአውድ-ኢንተርናሽናል ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ሙኒብ በበኩላቸው ለበዓሉ የሚገቡ እንግዶችን መቀበል መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

እንግዶቹ የሃዋሳ ቆይታቸው በጥሩ ስሜት የታጀበ እንዲሆን ለማድረግ የሆቴሉ ባለሙያዎች  የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን አልባሳት ለብሰው አቀባበል እያደረጉላቸው ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የሆቴሉ አቀባበል ኢትዮጵያዊነት በተላበሱ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

የበዓሉ በከተማው መከበር የሆቴል አገልግሎትን ጨምሮ የተለያዩ የስራ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የበዓሉ መከበር ኢትዮጵያ አንድነትን ለማጠናከር የሚያግዝ በመሆኑ እንግዶችን በተገቢው ማስተናገድ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በመሆኑ በተገቢው እንተገብረዋለን ብለዋል።

የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ በበኩሉ በሆቴሎችና አልጋ ቤቶች አካባቢ ለሚኖረው ጸጥታና በአገልግሎት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ለማድረግ ከንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡

የፖሊስ መምሪያው አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር መልካሙ አየለ እንደገለጹት፤ ለበዓሉ የሚገቡ እንግዶች የሚያርፉባቸው ሆቴሎችና አልጋ ቤቶች ሰላማዊ እንዲሆኑ ተገቢ ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡

በዓሉን አስመልክቶ ከተማዋን ለማስዋብ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ሲሆን ሆቴሎችም እንግዶችን መቀበል ጀምረዋል።