በቀጣይ አንድ ወር በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ፣ ፀሐያማ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ አመዝኖ ይቀጥላል – የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

412

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ህዳር 27/2015 በቀጣይ አንድ ወር በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ፣ ፀሐያማ እና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ አመዝኖ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ከምስራቅ አውሮፓ በመነሳት ወደ አገሪቱ በሚነፍሰው የሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት ምክንያት ደረቅና ቀዝቃዛ የአየር ፀባይ ከዕለት ወደ ዕለት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

ይህንን ተከትሎ በሰሜን ምስራቅ፣ በመካከለኛውና በምስራቅ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚጠናከር ይጠበቃል ብሏል።

በአንዳንድ ደጋማ ቦታዎች ደግሞ ውርጭ ሊያስከትል እንደሚችልም ነው ያመላከተው።

በጥቂት የምዕራብና የደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች፣ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ የሶማሌ ክልል የሊበንና የጎዴ ዞኖች ላይ ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚጠበቅም ትንበያው ያሳያል።

ቀሪ የአገሪቱ ክፍሎች በአብዛኛው ደረቃማ ሆነው እንደሚቆዩም ነው የተመላከተው።

የአየር ሁኔታው የመኸር ሰብል ስብሰባና ድህረ-ሰብል ስብሰባ ላይ ለሚገኙ አካባቢዎች የዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን አመቺ ስለሚሆን አርሶአደሮች ይህን ሁኔታ በመጠቀም በማሳ ላይ የሚገኙና የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እንዲያነሱም ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከደረቃማው የእርጥበት ሁኔታ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ የሰሜን ምስራቅ፣ መካከለኛውና ምስራቅ ደጋማ አካባቢዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ሊጠናከር እንደሚችልና ውርጭ የማስከተል አቅም እንደሚኖረውም ተገልጿል።

ይህም በመስኖ የሚለሙ ሰብሎች፣ አትክልቶች፣ የፍራፍሬ ተክሎችና በእንስሳት ጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው ስለሚችል አስፈላጊውን ዝግጅትና ጥንቃቄ እንዲደረግም ጠይቋል።

በጥቂት የምዕራብና የደቡብ ኦሮሚያ ዞኖች፣ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል የሊበንና ጎዴ ዞኖች የሚገኘው እርጥበት ለእንስሳት ልማት፣ ለሰብሎችና ቋሚ ተክሎች የተሟላ እድገት አዎንታዊ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።

የአየር ሁኔታው በአብዛኛው የአገሪቱ ተፋሰሶች ላይ የበጋው ደረቅና ከፊል ደረቃማ እንደሚሆን ይጠበቃልም ነው የተባለው።

በምዕራብ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ እንዲሁም ደቡብ ምስራቅ ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እርጥበት እስከ እርጥበታማ ሁኔታ እንደሚጠበቅም ተገልጿል።