የግብርና ውጤቶችና ቴክኖሎጂዎችን የሚያስቃኝ አውደ-ርዕይ በይፋ ተከፈተ

212

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 27 ቀን 2015  የግብርና ውጤቶችና ቴክኖሎጂዎችን የሚያስቃኝ አውደ-ርዕይ በይፋ ተከፈተ።

የግብርና ሚኒስትሩ  ዑመር ሁሴን ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን አውደ-ርዕዩን መርቀው ከፍተዋል።

ለሁለት ቀናት የሚቆየው አውደ-ርዕይ የግብርና ሚኒስቴር፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት ነው።

አውደ-ርዕዩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ  እየተካሄደ  ሲሆን ለውጡን ተከትሎ በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶች ቀርበዋል።

ሚኒስትሩ  ዑመር  ሁሴን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ግብርናው ለኢኮኖሚው  የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

በዚህም በዘርፉ ምን ያህል ርቀት ተጉዘናል? ምን ይቀራሉ? ክፍተቱ የቱ ጋር ነው ? መፍትሔውስ? የሚለውን በዝርዝር ለማየት አውደ- ርዕዩ ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ግብርናው የሚፈልገውና እየቀረበ ያለው እየተጣጣመ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ከአውደ-ርዕዩ ጎን ለጎን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ምክክር የሚደረግ ይሆናል ብለዋል።

ይህም በዘርፉ ያሉትን ችግሮችን ነቅሶ ለማውጣትና መፍትሔ ለማበጀት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።      

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ፤ አውደ-ርዕዩ በመንግሥትና በግል ተቋማት፣ በባንኮችና  በሌሎችም  የተከናወኑ የግብርና ውጤቶች የሚታዩበት ነው።  

ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት በሰብል ምርታማነት በእንስሳት ሀብት ልማትና በተፈጥሮ ጥበቃ ሥራዎች ትልቅ ውጤት መመዝገቡንም በዚሁ ጊዜ አንስተዋል።  

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቶ ኢስሙ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት 60 ዓመታት በግብርናው ዘርፍ  ከ3 ሺህ በላይ ቴክኖሎጂዎችን አፍልቋል።

በወቅቱ በሄክታር ከ5 ኩንታል ያልበለጠ ምርት ይሰበሰብ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ጊዜ  በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ምርት እየተሰበሰበ መሆኑ ከተገኙ ውጤቶች መካከል መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት 5 ዓመታት የተሻሻለ የስንዴ ዝርያ በመውጣቱም የስንዴ ምርታማነት ከፍ ማለቱን ጠቅሰው፤ ይህም በአውደ-ርዕዩ ላይ በማሳያነት  ቀርቧል።

በአውደ-ርዕዩ ላይ የተሳተፉ አቅራቢዎች  የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን ይዘው ቀርበዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ አቅራቢዎች በሰጡት አስተያየት፤ በግብርና ሥራዎች ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቢሆንም የፋይናንስ እጥረት ትልቅ ፈተና ሆኖብናል ብለዋል።      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም