የተቋቋመው የጸረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው -ምሁራን

153

ሀረር (ኢዜአ) ሕዳር 27 /2015  መንግስት የጸረ ሙስና ብሔራዊ  ኮሚቴ አደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱ  ሙስናን ለመዋጋት ያለውን  ቁርጠኝነት እንደሚያሳይና  ሊደገፍ እንደሚገባው የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንገለጹ።

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት  ዶክተር ተስፋዬ ለማ እንዳሉት "ሙስና  በዓለም ላይ ሰላም እንዳይኖርና ፍትህ እንዳይሰፍን ምክንያት እየሆነ የመጣ ነው"፡፡

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት  ዶክተር ተስፋዬ ለማ እንዳሉት "ሙስና  በዓለም ላይ ሰላም እንዳይኖርና ፍትህ እንዳይሰፍን ምክንያት እየሆነ የመጣ ነው"፡፡

በመንግስት "የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት" ያሉት ዶክተር ተስፋዬ፤  በተለይም በሙስና በሚሳተፉና በሁሉም እርከን ላይ ያሉ የየስራ ሃላፊዎች ላይም ለሌሎች  አስተማሪ የሆነ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የስነ ምግባርና  ጸረ ሙስና ዳይሬክቶሬት  ዳይሬክተር  አቶ ዘላለም ደሳለኝ በበኩላቸው "ሙስና እንደ ሀገር ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል" ብለዋል።

ያንን ለመቀልበስ የተቋቋመው የጸረ ሙሰና ብሔራዊ  ኮሚቴ መንግስት ሙስናን ለመዋጋት ያለውን  ቁርጠኝነት የሳየ በመሆኑ ሊደገፍ ይገባል ነው ያሉት።

ሙስና በአንድ አገር ላይ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል  እንዳይኖር በማድረግ  በማህበረሰቡ የእለት ተእለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ እያንዳንዱ ዜጋ ሙስናን  ሊታገለው እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

ብሄራዊ ኮሚቴው መቋቋሙ ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም ኮሚቴው መቋቋሙ ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛም ሆነ መላው ህብረተሰብ ለኮሚቴው መረጃ ማቀበልና ለውሳኔው በመገዛት  ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

"በአገራችን የሙስና ድርጊት እየተንሰራፋ ከመምጣቱና በህዝቡ ላይ እያሳደረው ካለው ጫና አንጻር ብሔራዊ ኮሚቴው መቋቋሙ ተገቢ ነው" የሚሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር አቶ ፍሬው ካሳዬ ናቸው፡፡

የሙስና ወንጀል መንሰራፋት የመንግስት እና የህዝብ  ተቋማት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር  የፍትህ ተቋማት ስራቸውን በተገቢው መንገድ እንዳያከናውኑ እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጡ በማድረግ ህዝብን ለምሬት የሚዳርግ ነውም ብለዋል፡፡

ሙስና በብር ብቻ ሳይሆን በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንደሚስተዋል ገልጸው፤ ሰዎች በብቃታቸው ሳይሆን   በትውውቅ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይቀጠራሉ፤ ህዝብም ለምሬት ይዳረጋል ብለዋል ፡፡

ሙስናን ለመዋጋት ተቋማትን በብቁ የሰው ሃይል ማደራጀት፤ ግልፅነትትና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ እንዲሁም  ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር  መብቱን የሚጠይቅ ትውልድ ማፍራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ማህበረሰቡም አገልግሎት ለማግኘት ሙስናን  እንደ አንድ አማራጭ ከመጠቀም ይልቅ መብቱን በመጠየቅ ለመንግስትም ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ምሁራኑ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም