ኢትዮጵያና ሩስያ በንግድና ምጣኔ ሃብት ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ

301

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 27 ቀን 2015 ኢትዮጵያና ሩስያ በንግድና ምጣኔ ሃብት ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ በጋራ እንደሚሰሩ ገለጹ።

ስምንተኛው የኢትዮጵያና ሩሲያ በይነ-መንግሥታዊ የሳይንስ፣ ቴክኒክ፣ ኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ማስጀመሪያ ወቅት የሁለቱ አገሮች ተወካዮች ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ማብራሪያ ሁለቱ አገራት  በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ በነበረችበት ወቅት ሩስያ ለነበራት አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል።

የመድረኩ ዓላማ አገራት በምጣኔ ሃብት፣ በሳይንስ፣ በንግድና ሌሎች ዘርፎች ጠንካራ ውይይት በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነትን አውድ ለመፍጠር መሆኑን አስረድተው ሁለቱ አገሮች ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ  መድረኩ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የባዮሎጂካል ማዕከል ለማቋቋም፣ ኒኩሊየርን ለሰላማዊ አገልግሎት ለማዋልና በሌሎች መስኮች  በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጨምረዋል።

በመድረኩ በሰባተኛው ስብሰባ በጋራ የተደረሱ የስምምነት ነጥቦች አፈጻጸምን በመገምገም፣ አዳዲስ የትብብር መስኮችን በመለየት ከስምምነት የሚደረሱና ቀጣይ የሚደረጉ እንዳሉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተሪክሂን ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ነባራዊ ሁኔታ በምጣኔ ሃብት ዘርፍ በስፋት ለመተባበር ችግር ፈጥሮ እንደነበር አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት መንግሥት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት በምጣኔ ሃብትና ሌሎች ዘርፎች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል።

ሩስያ ለባልቻ ሆስፒታል የምታደርገውን ድጋፍ ለቀጣይ 25 ዓመታት ማራዘም የሚያስችል ስምምነት እንደሚደረግም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

የሩስያ የማዕድን ሃብት ፌደራል ኤጀንሲ ኃላፊ ኢዩጌኒ ፔትሮቭ በበኩላቸው፤ በውይይቱ በንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ሌሎች የኢኮኖሚ ትብብሮች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡

ለሦስት ቀናት በሚካሄደው የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ 50 የሩስያ ሉዑክ አባላት፣ የኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ፣ ሕዋ ሳይንስ፣ ኮሙኒኬሽን፣ ማዕድን፣ ትራንስፖርትና ሌሎች ተቋማት ተወካዮች እና የግሉ ዘርፍ እየተካፈሉ ይገኛሉ፡፡