የሰላም ስምምነቱ ምርቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በሁሉም አካባቢዎች እንዲደርሱ በማድረግ የሎጂስቲክስ ዘርፉ እንዲሻሻል ያደርጋል

266

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ሕዳር 27 ቀን 2015 የሰላም ስምምነቱ ምርቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በሁሉም አካባቢዎች እንዲደርሱ በማድረግ የሎጂስቲክስ ዘርፉ እንዲሻሻል እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ፡፡

መንግስትና ህወሃት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በኬንያ ደግሞ ስምምነቱን መፈጸም የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ይሄንን ተከትሎ በተለይም የግጭት ስጋት የነበረባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች የሰላም አየር መተንፈስ ጀምረዋል፤ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ጥያቄዎቻቸውም ምላሽ እያገኙ ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ ለማዳረስ ሰላም ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ተከስቶ የነበረው ግጭት የድርጅቱን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጥሮ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

በመላ ሀገሪቱ መዳረሻዎች እንዳለው ተቋም ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ምርቱን ከቦታው ለማድረስ ሰላም ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ ሰላማዊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተፈጥሮ ደህንነቱ የተጠበቀ ምርት ለተጠቃሚው ለማድረስ ገንቢ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

"የሰላም እጦት ያደረሰብንን ጉዳት ጠንቅቀን እናውቀዋለን" ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በኢትዮጵያ ግጭቱ ቆሞ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ላደረጉ አካላት የላቀ አክብሮት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ለልማት ሰራዎች መሳለጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ለኢትዮጵያ ልማት የሚጠበቅብንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን" ብለዋል፡፡

የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በመላ ሀገሪቱ ለመስራት ያሰባቸው የልማት ስራዎች ተግባራዊ ለማድረግ ምቹ እድል እንደሚፈጥርም አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪ የግንባታ ስራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የሰላም ስምምነቱ ይዞልን የመጣውን እድል በአግባቡ እንጠቀምበታለን ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም