8ኛው የኢትዮ-ራሺያ የበይነ መንግስታዊ የትብብር መድረክ በአዲስ አበባ ተጀመረ

151

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ሕዳር 27 /2015 8ኛው የኢትዮጵያ እና የራሺያ በይነ መንግስታዊ የሳይንስ፣ የቴክኒክ፣ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር መድረክ በአዲስ አበባ መካሔድ ጀመረ።

በመድረኩ ማስጀመሪያ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ኢትዮጵያ እና ራሽያ ያላቸውን ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት አንስተዋል።

ራሺያ በሳይንስ፣ በትምህርትና ሌሎች ዘርፎች ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ድጋፍ በማመስገን በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

መድረኩ ሳይንስ፣ ቴክኒክ፣ ኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች የሚያጠናክሩበት እንደሚሆን ገልጸዋል።


ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች ባለው የአገር በቀል ምጣኔ ሀብት በማዕድንና ሌሎች ዘርፎች ያሉ አማራጮች ላይ የራሺያ ባለሀብቶች ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።


በኢትዮጵያ የራሽያ አምባሳደር ኢቨገንሲ ተርክኒን በበኩላቸው መድረኩ የተደረጉ ስምምነቶችን በተግባር ለመቀየር፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመጨመር ምክክር የሚደረግበት እንደሚሆን አንስተዋል።

በመድረኩ ከፍተኛ የራሺያ መንግስት ባለስልጣናትና ዲፕሎማቲክ ልዑካን የተገኙ ሲሆን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች፣ ከንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ይመክራሉ ተብሏል።

መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ሁለቱ አገሮች በሳይንስ፣ ቴክኒክ፣ ኢኮኖሚ እና የንግድ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር የበለጠ በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በተመሳሳይ አገራቱ በጋራና በተናጠል ሊያከናውኗቸው ያቀዷቸው ጉዳዮች በማቅረብ ከዚህ ቀደም የገቧቸውን ስምምነቶች ውጤት ይገመግማሉ።


7ኛው የኢትዮ ራሺያ በይነ መንግስታዊ የትብብር መድረክ በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ራሺያ መካሔዱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም