በዘንድሮው የመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነው መሬት እስካሁን ከ42 በመቶ በላይ የሚሆነው ምርት ተሰብስቧል

117


አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 26/2015 በ2014/15 ምርት ዘመን በመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነው 13 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ ከ42 በመቶው በላይ የሚሆነው መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢሳያስ ለማ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በምርት ዘመኑ በመኸር ወቅት 400 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል።

ምርቱን ለማግኘት 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር ላይ የነበረው ምርት ተሰብስቧል።

በዘመናዊ እና በባህላዊ የምርት መሰብሰቢያ መንገዶች በመታገዝ ከ42 በመቶ በላይ የሚሆነው ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።

ምርታማነትን ለመጨመር 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የእርሻ አስተራረስ ዘዴ መታረሱን አስታውሰው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ሂደት እየተሻሻለ መምጣቱን እና 3 ሚሊየን ሄክታር የሚሆን መሬት በትራክተር መታረሱንም ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በተወሰኑ ሰብሎች ብቻ በኩታ ገጠም ይዘራ የነበረውን አሰራርም በዚህ ዓመት ወደ አሥር የሰብል ዓይነቶች ማሳደግ መቻሉን አስታውቀዋል።

በዘንድሮው የምርት ዘመን የተሻለ ዝግጅት የተደረገበትና ጥሩ የአየር ንብረት ስለነበረው ከዕቅዱ በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖች በተሻለ መልኩ ሥራ ላይ እንዲውል እየተደረገ መሆኑን ገልጸው የምርት ብክነት በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

ለዚህም ለአርሶ አደሮች የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሰራታቸውንና በዚህም ጥሩ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን በመግለጽ።

በተለይ ከሁለት ዓመት ወዲህ ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ብድር በመመቻቸቱ ጥሩ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ መጋዘኖችን በማጽዳት ምርት እንዳይበላሽ በማድረግ ምርቱን ከብክነት የመታደግ ሥራዎችን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።

እንደ አገር በሰብል ምርት ራስን ለመቻል የተያዘውን ግብ ለማሳካት ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም