ወጣቱ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር ኢቫን ባርቶን በዓለም ዋንጫ

188

በኳታር አስተጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ዛሬ 16ተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ 36 ዋና ዳኞች፣69 ረዳት ዳኞች እና 24 የቪዲዮ ረዳት ዳኞች እንዲያጫውቱ መመደቡ ይታወቃል።

ከዋና ዳኞቹ መካከል ኤል ሳልቫዶራዊው ኢቫን ባርቶን ይገኙበታል።

ኢቫን አርቺዴስ ባርተን ሲስኔሮስ እ.አ.አ ጥር 27 ቀን 1991 በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ኦሬንጅ ካውንቲ(አውራጃ) በምትገኘው ሳንታ አና ከተማ ከኤልሳልቫዶራዊያን ቤተሰቦቻቸው ተወለዱ።

ሳንታ አና ቀደምት የአሜሪካ ነዋሪዎች(ኔቲቭ አሜሪካንስ) ከሚኖሩባቸው የአሜሪካ አካባቢዎች መካከል አንዷ ናት።

ኢቫን ዳኝነትን የጀመሩት “ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ዲ ፉትቦል ዲ ኤል ሳልቫዶር” የሚል ስያሜ ባለው የአገሪቷ የእግር ኳስ ሊግ ነው።

የሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ እና ካሪቢያን ሀገራት ኮንፌዴሬሽን(ኮንካካፍ) ውድድሮች ላይ አጫውተዋል።

እ.አ.አ. 2019 በኮንካካፍ ጎልድ ካፕ ጃማይካና አሜሪካ ያደረጉትን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በመሐል ዳኝነት የመሩበት ጨዋታ ይጠቀሳል።

ኢቫን እ.አ.አ 2018 በ27 ዓመታቸው በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ተመዝገበው ኢንተርናሽናል ዋና አርቢትር ለመሆን በቁ።

እ.አ.አ. በ2019 ብራዚል አስተናግዳ ብራዚል በበላችው 18ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ተመርጠው ስፔን ከታጂኪስታን እንዲሁም ብራዚል ከፈረንሳይ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች በመሐል ዳኝነት መርተዋል።

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ በዋና ዳኝነት እንዲያጫውቱ ከማዕከላዊ አሜሪካ ሶስት ዳኞችን ሲያሳውቅ  ኤል ሳልቫዶራዊውን ኢቫን ባርተን ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድሩ ላይ እንዲያጫውቱ መረጣቸው።

ማሪዮ ኤስኮባር ከጓቲማላ እንዲሁም ሳይድ ማርቲኔዝ ከሆንዱራስ ሌሎች ከማዕከላዊ አሜሪካ የተመረጡ ዳኞች ናቸው።

ኢቫን ባርተን በዓለም ዋንጫው የሞት ምድብ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በነበረው ምድብ አምስት ጃፓን ጀርመንን 2 ለ 1 በማሸነፍ ያልተጠበቀ ውጤት ስታስመዘግብ እና በምድብ ሰባት የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ብራዚል ስዊዘርላንድን በጠባብ ውጤት1 ለ 0 ስትረታ በመሐል ዳኝነት መርተዋል።

ትናንት በአል በይት ስታዲየም እንግሊዝ ሴኔጋን በጥሎ ማለፍ ጨዋታ 3 ለ 0 ያሸነፈችበትን ጨዋታ በዋና ዳኝነት አጫውተዋል።

በዓለም ዋንጫው ዛሬ እንግሊዝና ሴኔጋል የሚያደርጉትን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ይመራሉ።

የ31 ዓመቱ ኢቫን ባርተን ከፕሮፌሽናል እግር ኳስ ዳኝነታቸው ውጪ የኬሚስትሪ ባለሙያ ናቸው።

በአንጋፋውና በግዙፋ የኤል ሳልቫዶር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኬሚካል ሳይንስ አግኝተዋል።

ትምህርታቸውን በዩኒቨርሲቲው በመቀጠል “ኦርጋኒክ ኬሚስትሪ” በሚል የትምህርት ዘርፍ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።

ኢቫን በሙያ ዘርፋቸው የተለያዩ የጥናትና ምርምር ስራዎችንም አከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም