በአገሪቱ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አረጋውያን ድጋፍ ይሻሉ

75
አዲስ አበባ መስከረም 18/2011 በኢትዮጵያ ከ4ነጥብ5 ሚሊዮን በላይ አረጋውያን በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሄራዊ ማህበር ጋር በመሆን መስከረም 21 ቀን 2011 ዓ.ም ለ27ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአረጋውያን ቀንን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ይርጋለም እንደገለጹት፤ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን የጤና አገልግሎት፣ የመጠለያ፣ የመሰረታዊ ፍጆታና የህግ ከለላ ድጋፍ በጊዜያዊነትና በዘላቂነት ያስፈልጋቸዋል። ከመሬት ይዞታ ባለቤትነት ጋር በተያያዘም አረጋውያኑ የተለያየ ችግር የሚገጥማቸው እንደሆነና በልማት ሲነሱም ተመጣጣኝ የሆነ የካሳ ክፍያ የማያገኙ እንደሆነ ጠቁመዋል። አረጋውያኑ ለተለያየ ችግር በመጋለጣቸውና ለችግሮቻቸው መፍትሄ ባለማግኘታቸው ከቄዬአቸው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመፍለስ ኑሯቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ እየመሩ እንደሆነም ጠቁመዋል። ችግሮቻቸውን በዘላቂነት ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር ለመስራት የሚያስችለው የአሰራር ስርዓት ቢዘረጋም ተቋማት አረጋውያንን ለመደገፍ የሚሰጡት ምላሽ ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል። መንግስትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተቀናጅተው አረጋውያንን በጊዜያዊነትና በዘላቂነተ ለመደገፍ የሚችሉበት ህጋዊ መሰረት መጣል እንደሚገባው ገልጸዋል። አረጋውያንን በመደገፍ ተጠቃሚ ለማድረግ ተቋማት ከሚኒስቴሩ ጋር በመሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ አረጋውያንና ጡረተኞች ብሄራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ በበኩላቸው ለአረጋውያን የጤናና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ፕሮግራም በሚፈለገው ልክ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳልሆነ ገልጸዋል። በዋናነት ከአገሪቱ እድገትና ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ አረጋውያን ለተለያዩ የጤና እክሎች ከመዳረጋቸው ባሻገር ኑሯቸውን ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ይመራሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ለአረጋውያን ክብር በቂ የኑሮ ደረጃ፣ የጤናና የማህበራዊ አገልግሎቶች የማግኘትና የመሳተፍ መብት እንዳላቸው ቢያስቀምጥም በኢትዮጵያ ተደራሽነቱ ዝቅተኛ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ አመልክተዋል። በዚህም አረጋውያንን ለመደገፍ በዓመት አንድ ጊዜ የአረጋውያን ቀን መታሰብ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ለመደገፍ ሁሉም ባለድርሻ አካል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል። ዘንድሮ የአረጋውያን ቀን የሚከበረው ''ቀደምት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን በመዘከር የኢትዮጵያ አረጋውያንን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እናረጋግጥ'' በሚል መሪ ሃሳብ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም