በመንግስት የሚከናወኑ የመልሶ ግንባታ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድርሻችንን እንወጣለን - ነዋሪዎች

187

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 25/2015 በመንግስት የሚከናወኑ የመልሶ ግንባታ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የራያ ቆቦ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል በነበረው ግጭት የተጎዱ መሰረተ ልማቶች መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ መንግስት የመልሶ መገንባትና የማቋቋም ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም የፕሮጀክቶቹ ፈጥኖ መጠናቀቅ ጥቅሙ ለራሳቸው እንደመሆኑ ለግንባታው መፋጠን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በራያ ቆቦ ወረዳ የወርቄ 02 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ጥሩዬ መንገሻ "የጦርነት ጊዜው አልፎ ፊታችንን ወደ ልማት ያዞርንበት ጊዜ ማየቱ ብቻ ትልቅ ድል ነው" በማለት ገልጸዋል።

በአካባቢያችን የተጀመሩትን የጤና ጣቢያ፣ የትምህርት ቤት፣ የጤና ኬላና ሌሎች ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅም "ድንጋይ፣ አሸዋና ለሰራተኞች ቀለብ በማቅረብ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን" ብለዋል።

የክልሉ መንግስት እንደ ጤና ጣቢያ፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊንክ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ፕሮጀክቶችን መልሶ በማስጀመሩ ደስታ እንደተሰማቸው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ይማም ተስፉ ገልጸዋል።

የክልል፣ የዞንና የወረዳው ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በቦታው በመገኘት የተጎዳውን ማህበረሰብ ወደ ልማት እንዲዞር ለማነቃቃት ያደረጉት እንቅስቃሴም መልካም መሆኑን ገልፀዋል።

በአካባቢያቸው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በአካባቢው ተገኝተው በርካታ ፕሮጀክቶችን ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፤ መንግስት በጦርነት የወደመውን አካባቢ ደረጃ በደረጃ መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም ቁርጠኛ አቋም ወስዶ እየሰራ ነው ብለዋል።

"ጀግንነት በጦርነት ብቻ ሳይሆን በልማት ድህነትን ድል መንሳት ጭምር ነው" ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የአካባቢው ህዝብም በልማት ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ አሳስበዋል።

በተለይም በተያዘው በጋ ሁሉንም የውሃ አማራጮች በመጠቀም በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ በማምረት የራሳቸውንና የአካባቢያቸውን የኑሮ ሁኔታ ለመለወጥ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የክልሉ መንግስትም ያስጀመራቸውን የተቋማት ግንባታ በዚህ ዓመት ከማጠናቀቅ ባሻገር በመስኖ ልማት ለሚሰማሩ ለአካባቢው ወጣቶች የውሃ መሳቢያ ሞተር በስጦታ ለማበርከት ቃል ገብተዋል።

የክልሉ መንግስት በዘንድሮው ዓመት ለሚካሄደው የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራ አንድ ቢሊየን ብር መድቦ ወደ ተግባር መግባቱን መግለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም