ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አንድነት የመኪና ማቆሚያን መርቀው ከፈቱ

796

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 25/2015 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአዲስ አበባ የተገነባውን አንድነት የመኪና ማቆሚያ መርቀው ከፈቱ።

የመኪና ማቆሚያው ዘመናዊ ሲሆን አጠቃላይ ሥፋቱ 1 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት፣ ወደታች እስከ 4 ደረጃ ወለል ድረስ ለመኪና ማቆሚያ የተዘጋጀ ነው።

መጀመሪያ ወለል ላይና ከታች ባሉ አራት ተከታታይ የምድር ወለሎች አውቶቡሶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 1 ሺህ 20 ተሸከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ይችላል፡፡

የመኪና አሳንሰር የተገጠመለት፤ አሳንሰ‍ሩ ከወለል በታች ያሉ የማቆሚያ ቦታዋች ጋር በቀላሉ ያስተሳሰረ ሲሆን ለመኪና መቆጣጠሪያነት ከ200 በላይ ካሜራዎች አሉት።

ካሜራዎቹ እንደ አስፈላጊነቱ የመኪናን መለያ ሰሌዳ እንዲሁም የተገልጋዩን ማንነት ይለያሉ ነው የተባለው።

አንድነት የመኪና ማቆሚያ ዘመናዊ የተሸከርካሬዎች መረጃ መመዝገቢያና መስጪያ፣ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት፣ የደህንነት መጠበቂያ ሥርዓቶች የተሟላለት ነው፡፡

ምድር ቤትና ከላይ ባሉት ተከታታይ አራት ወለሎች ለቱሪዝምና መሰል የአገልግሎት ዘርፍ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጁ ከ150 በላይ ክፍሎችም አሉት፡፡

105 ሜትር ርዝመት፣ ስምንት ሜትር ስፋት እና 5 ሜትር ጥልቀት ያለው ወደ አንድነት ፓርክ መግቢያና መውጪያ የሚሆን ውብና ዘመናዊ መተላለፊያ አለው፡፡

የአምፊቲያትር ቦታው ለመሰብሰቢያ፣ የጥበብ ትርኢቶችና ሌሎች ዝግጅቶችን ሊያሰተናግድ ይችላል ተብሏል፡፡

ይህንኑ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዛሬው እለት በይፋ መርቀው ስራ አስጀምረውታል።