የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያን አምቅ መስህቦች በማስተዋወቅ አብሮነትን እያጸናን የምንቀጥልበት ነው-ምክትል አፈ-ጉባኤ ፈይዛ መሐመድ

170

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 25/2015 የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያን አምቅ መስህቦች በማስተዋወቅ አብሮነትን እያጸናን የምንቀጥልበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ተናገሩ።

የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ "ህብረ ብሄራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የባህል ፌስቲቫል ተካሂዷል፡፡

በፌስቲቫሉ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች የሚወክሉና ገላጭ የሆኑ አልባሳት፣ የተለያዩ ጌጣጌጦችና ባህላዊ ውዝዋዜዎች ለእይታ ቀርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ፈይዛ መሐመድ፤ የብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተናግረዋል።

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚሳተፉ ወገኖች ባህልና እሴቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበትና አንድነታቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩበት ሁነት መሆኑን ገልጸዋል።

የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዘቦች ቀን የኢትዮጵያን አምቅ መስህቦች በማስተዋወቅ አብሮነትን እያጸናን የምንቀጥልበት ልዩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የከተማ አስተደዳሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀንኣ ያደታ በበኩላቸው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለአገር ዘላቂ ሰላም፣ የጋራ ልማትና አብሮነት መጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 29 ቀን በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ የሚከበር ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም