ሰው አልባ አውሮፕላን ለህክምና ተግባር አገልግሎት ላይ ሊውል ነው

66
አዲስ አበባ መስከረም 18/2011 በኢትዮጵያ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በመጠቀም የህክምና መገልገያዎችን ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለማጓጓዝ እየተሰራ ነው። የዚህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ ደምን ጨምሮ የክትባትና ሌሎች መሰረታዊ መድሃኒቶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በተቻለ ፍጥነት ወደሚፈለግበት ስፍራ ለማጓጓዝ የሚያስችል ዓይነተኛ የትራንስፖርት አውታር ነው። ትራንስፖርቱ በተለይ ርቀት ወዳለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች በቀላሉና በሚፈለገው ፍጥነት ለመድረስ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለውም ይነገራል። በመሆኑም ከሁለት ቀናት በኋላ አምስት ኪሎ ግራም ክብደት ያለውን የክትባት መድሃኒትና ደም የጫነ የሙከራ በረራ ይከናወናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለኢዜአ አስታውቋል። የሙከራ በረራው ከቢሾፍቱ አየር ኃይል ተነስቶ መድረሻውን አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንደሚያደርግ በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ በላይነህ አያሌው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የሰው አልባ አውሮፕላን ትራንስፖርትን ለህክምና አገልግሎት ለመጠቀም የሚያስችለውን መርሃ-ግብር የሚተገብረው ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው፡፡ የበረራ መርሃ-ግበሩ ተግባራዊ ሲሆን የጭነት መጠኑ እንደየሁኔታው የሚጨምር መሆኑም ተገልጿል። ቴክኖሎጂውን በቋሚነት ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት በሁለቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች መካከል እንደሚፈረም ባለሙያው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም