በእንስሳት ምርታማነት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

275

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 25 ቀን 2015 የእንስሳት ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የእንስሳት ዘርፍ ኃላፊ ቶሌራ ደበላ፤ በክልሉ ያለውን ሰፊ የእንስሳት ሃብት ምርታማነት ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በ2014 ዓ.ም 321 ሺህ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ መደረጉን ጠቅሰው በዘንደሮው በጀት ዓመትም ከ520 ሺህ በላይ ምርታማ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ይደረጋል ብለዋል።

በንብ ሃብት ልማትም ከ100 ሺህ በላይ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሩ በማድረስ ከ60 ሺህ በላይ አናቢዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በቆላማ አካባቢዎች የሚስተዋለውን ድርቅ ለመቋቋም በሚደረግ ጥረትም በመስኖ እና በዝናብ ውጤታማ የመኖ ልማት እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት እውን ለማድረግም ወጣቶችን በማደራጀት በስጋ እና እንቁላል ዶሮ ልማት ውጤት እንዲያመጡ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የእንስሳት ሃብት ልማትን ለማሳደግ የሚደረገው የልማት እንቅስቃሴ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በመከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

የኦሮሚያ ክልል የእንስሳትና አሳ ሃብት ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ደረጄ ጉደታ፤ በክልሉ በሚገኙ 23 ወረዳዎች በተከናወነ የወተት ላም፣ ዶሮ፣ የስጋ እና የዓሳ እርባታ ልማት ላይ ተጨባጭ ውጤት እየመጣ ነው ብለዋል።

በዚህም ከ65 ሺህ በላይ ዜጎችን በማደራጀት ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን ገልጸዋል።

በተከናወነ የልማት ስራም የጋራ ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች በማደራጀት ከማህበራት እስከ ዩኒየን የደረሱ አምራች ዜጎችን ማፍራት እየተቻለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ የገንዘብ፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናን ጨምሮ የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፎች በመደረግ ላይ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም