በዓሉ ለህዝቦች የእርስ በርስ ትስስር መጠናከር ጉልህ ድርሻ አለው - የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ

155

ሀላባ ቁሊቶ (ኢዜአ) ህዳር 25/2015 የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለህዝቦች ትስስር መጠናከር ጉልህ ድርሻ እንዳለው የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ ገለጹ።

17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ''ህብረ ብሄራዊ አንድነት ለዘላቂ ሠላም'' በሚል ሀሳብ በደቡብ ክልል ሀላባ ቁሊቶ ከተማ እየተከበረ ነው።

ብዝሃነትን በአግባቡ በማስተናገድ እንደቀድሞ አባቶች እጅ ለእጅ ተያይዘን መቆም አለብን ሲሉ ገልጸዋል።

በተለይም ከ''የኔነት'' ይልቅ የ''እኛነትን'' አተያይ በማጉላት አብሮነትን ማጠናከር ይገባናል ነው ያሉት።

ህብረ-ብሄራዊ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በመገንባት ለሠላምና ልማት ምቹ ምህዳር በማስፋት የሀገራችንን ከፍታ ልናረጋግጥ ይገባል ብለዋል።

እንደሀገር እየተካሄደ የሚገኘው የዘላቂ ሠላም እሴት ግንባታ ከግብ ለማድረስ አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ በመክፈል በጋራ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል  ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ በበኩላቸው የቀኑ መከበር ብዝሃነታችንና ባህሎቻችን ጎልተው እንዲወጡ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የታደሙት የአፋር፣ የሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ምክር ቤቶች አፈ-ጉባኤዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም