የስፖርት ውድድሮች ማህበራዊ ትስስርንና አንድነትን ለማጠናከር የጎላ ፋይዳ አላቸው- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ውድድሮች ማህበራዊ ትስስርንና አንድነትን ለማጠናከር የጎላ ፋይዳ አላቸው- የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

ጂንካ (ኢዜአ) ህዳር 25 ቀን 2015 ዘመናዊ እና ባህላዊ የስፖርት ውድድሮች ፍቅርን፣ ወንድማማችነትን፣ ማህበራዊ ትስስርንና አንድነትን ለጠናከር የጎላ ፋይዳ እንዳላቸው የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ገለጹ።
በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ በሁለቱም ፆታዎች ታዋቂ አትሌቶች የተሳተፉበት የ8 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ዛሬ ተካሄዷል።

ለአሸናፊ አትሌቶች የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳለያ ሽልማት ያበረከቱት ሚኒስትሩ ይህንን በዘላቂነት ለማስቀጠል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማስፋፋት ይገባል ብለዋል።
የጎዳና ላይ ሩጫው በአለም ላይ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ማውለብለብ የሚችሉ ተተኪ አትሌቶች እንዳሉ ተመልክተናል ያሉት አቶ ቀጄላ፤ አትሌቶቹን ለማብቃት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው ዞኑ የበርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮዊ ፀጋ ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።
እንዲህ ዓይነቱ ህዝባዊ የስፖርት ውድድር በከተማዋ መካሄዱ በዞኑ ያሉትን የቱሪስት ሀብቶችና ቅርሶችን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የፋን ኢትዮጵያ መስራች እና የውድድሩ አዘጋጅ አትሌት ፋንቱ ሚጌሶ የቱሪስት መዳረሻ በሆነው ደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ውድድሩን በማሰናዳታችን ትልቅ ኩራትና ደስታ ይሰማናል ስትል ገልጻለች።
በደቡብ ኦሞ ዞን በአትሌቲክስ ላይ በትኩረት ከተሰራ በርካታ ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት እንደሚቻል ጠቁማ ለዚህም እንዲረዳ በዞኑ የአትሌቲክስ ማዕከል ለማቋቋም መታቀዱን ይፋ አድርጋለች።