ግምቱ ከ8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ልባሽ ጨርቅ ሲያጓጉዙ የነበሩ ግለሰቦች ተያዙ

306

አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 25/2015 ግምቱ ከ8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ልባሽ ጨርቅ ሲያጓጉዙ የነበሩ አሽከርካሪና ረዳቱ መያዙን የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ እንደገለፁት ግለሰቦቹ የተያዙት ትላንት ከቀኑ 11:00 ሰዓት ላይ ነው።

ግለሰቦቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-A03701 ኢ.ት በሆነ ተሳቢ ሎቤድ ተሽከርካሪ 299 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅ በኮንቴነር ጭነው ከድሬዳዋ ወደ አዳማ በመጓዝ ላይ እንዳሉ መያዛቸውን ተገልጿል።

በአዳማ ከተማ ዳቤ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ኩርፋ በተባለ የፍተሻ ኬላ የፀጥታ ሃይሎች ባደረጉት ፍተሻ መያዛቸውን ጠቁመው አሽከርካሪውና ረዳቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ምክትል ኢንስፔክተር ወርቅነሽ አመልክተዋል።

የተያዘው የኮንትሮባንድ ልባሽ ጨርቅ ከ8 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለውና 23ሺህ 490 ኪሎ ግራም የሚመዝን መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ልባሽ ጨርቁ በኢትዮጵያ ጉሙሩክ ኮሚሽን ለአዳማ ቅርንጫፍ ገቢ መደረጉን ምክትል ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም