24ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ጠቅላላ ስብሰባ እየተካሄደ ነው

302

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 25/2015 24ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት ጠቅላላ ስብሰባ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ስብሰባው በሽብር ወንጀል፣ በሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ በአደንዛዥ ዕፅ፣ በእንስሳት ዘረፋ እና በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘለላም መንግስቴ፤ የህብረቱ የስራ ኃላፊዎች፣ የቀጣናው ኢንተርፖል ኃላፊዎች፣ አታሼዎች፣ የየአገራቱ የፖሊስ አዛዦች በስብሰባው እየተሳተፉ ይገኛሉ።

23ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኪንሻሳ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።

ኢትዮጵያም የህብረቱን ስብሰባ ስታዘጋጅ የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከዚህ ቀደም በ2008 ዓ.ም ስብሰባውን ማስተናገዷ ይታወቃል።

ተቀማጭነቱን በኬኒያ ናይሮቢ ያደረገው ህብረቱ በምስራቅ አፍሪካ አገራት የሕግ አስከባሪ ተቋማትን ትብብር ለማጠናከር፣ መረጃ ልውውጥ ለማጎልበት፣ የጋራ ስትራቲጂ ለመንደፍ እና በቀጣናው ሰላም ለማስፈን የሚሰራ መሆኑም ተገልጿል።

ህብረቱ በተለይም ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመመከት ግብ ይዞ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1998 በኡጋንዳ ካምፓላ ነው የተቋቋመው።

ህብረቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሲሸልስ፣ ሩዋንዳ፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኮሞሮስና ቡሩንዲ በአጠቃላይ 14 አገራትን በአባልነት ያቀፈው ነው።

የህብረቱ ስብሰባም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ እንደሚቀጥል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም