ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሰልጣኞች የሰላም አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ ተጠየቀ

117

ሀዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 24 ቀን 2015 የ5ኛ ዙር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሰልጣኞች በየተሰማሩበት አካባቢ የሰላም አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም አሳሰቡ።

የሰላም ሚኒስቴር ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም "በጎነት ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ከ6 ሺህ 630 በላይ ወጣቶችን ዛሬ አስመርቋል።

በተመሳሳይ መርሃ ግብር በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲም በበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት የሰለጠኑ 1ሺህ 330 የሚበልጡ ወጣቶች ተመርቀዋል።

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም በምረቃ ሥለሥርዓቱ ላይ በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት የዕለቱ ተመራቂዎች ተመድባችሁ በምትሄዱባቸው አካባቢዎች በዋናነት እንድትሰሩ የሚጠበቅባችሁ ስለሠላም መስበክና ማስተማር ነው ብለዋል።

እንዲሁም በምትሄዱበት ስፍራ ሁሉ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምንና አብሮነትን በማስረፅ ለዚህ ዓላማ መሰለፋችሁን በተግባር ማረጋገጥ ይጠበቅባቸኋል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች መለያየትን፣ በበጎ አለመተያየትን፣ አንዱ ሌላውን በጠላትን የሚፈርጁ የተሳሳቱና የተዛቡ ትርክቶች መዘራታቸውን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

የዕለቱ ምሩቃን ወጣቶች ይህን የተሳሳተ ትርክት የማረምና የማስተካከል ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ተገንዝበው ህዝቡን በቅርብ ሆነው በማስተማር የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

የዘንድሮው የ5ኛ ዙር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሰልጣኞች በየተሰማሩበት አካባቢ የሰላም አምባሳደር ሆነው መንቀሳቀስ የመጀመሪያውና ቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይህን መርሃ ግብር ሀገራቸውን ለማወቅ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።

መርሃ ግብሩ ተመድበው የሚሄዱበትን አካባቢ ማህበረሰብ አኗኗር፣ ስነልቦና፣ ባህልና ቋንቋ ለማወቅ እድል እንደሚፈጥርላቸውም ገልጸዋል።

መንግሥት የሰጣቸውን ከፍተኛ ኃላፊነትና ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግ እንዲተጉ አስገንዝበዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ደመቀ አጭሶ በምረቃ ሥነሥርዓቱ ላይ እንዳሉት የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ኢትዮጵያዊ እሴቶችንና መርሆችን ለወጣቱ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የላቀ ድርሻ አለው።

እንዲሁም በዘር፣ በጎሳ፣ በሃይማኖትና በሌሎችም ማንነቶች ላይ መሠረት አድርጎ ያለውን መከፋፈልና ጥርጣሬ ለማስወገድ ገንቢ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸዋል።

በዚህ ሂደትም ወጣቶች ማህበራዊ እሴቶችን እና የሞራል አቅም እንዲያጎለብቱ እንደ ሀገር እርስ በርስ መደማመጥና መረዳዳትን እንዲያጸኑ አዎንታዊ ድርሻ እንዳለው ጠቁመዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ እንዳሉት የብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት አንዱ የሌላውን እሴቶችንና ባህል እንዲያውቅና እንዲያከብር ገንቢ ሚና ይጫወታል።

"በተለይ ከተዘራብን ጭፍን ጥላቻ ወጥተን እርስ በርስ የተጋመድን ማህበረሰብ እንዲፈጠር በማድረግ ለዘላቂ ሰላምና ለሀገራዊ መግባባት ምሶሶ ነው" ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል።

ዩኒቨርሰቲው በ5ኛው ዙር በወጣቱ ምክንያታዊነትና በሀገር ግንባታ ላይ ያተኮረ የአንድ ወር ስልጠና መስጠቱን ጠቅሰው፤ ይህም የስራ ባህልን ለማጎልበትና ማህበራዊ ትስስርን ለማስፋፋት ወሳኝነት መሆኑን አስረድተዋል።

በዩኒቨርስቲው የ5ኛ ዙር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ አገልግሎት ሰልጣኞች መካከል ቃልኪዳን ጌታቸው እና ቢንያም ተስፋዬ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በስልጠና ቆይታቸው ከራሳቸው አልፈው ለሀገራቸው አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚያስችል የሥራ ፈጠራ ክህሎትና እውቀት መቅሰማቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ በሚሰማሩበት በማናቸውም ስፍራ ሀገራዊ እሴቶችን የሚያጎለብቱጉ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን የሚያፋጥኑ ተግባራትን በማከናወን ማህበረሰባቸውን ለማገልገል መነሳሳታቸውን ገልጸዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ብሄራዊ የበጎ ፈቃድ ማህበረሰብ ልማት አገልግሎት ፕሮግራም "በጎነት ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ የሰለጠኑ ወጣቶች ዛሬ ያስመረቀው በወላይታ ሶዶ፣ በዋቻሞ፣ በጅማ፣ በደብረ ማርቆስና በባህርዳር ዩኒቨርስቲዎች ነው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም