ዳያስፖራው የሚያደርገው ተሳትፎ መነሻውም መድረሻውም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው - የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት

131

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 24/2015 ዳያስፖራው የሚያደርገው ተሳትፎ መነሻውም መድረሻውም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ ከ26 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ 700 የሚደርሱ ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ወደ ሀገር ውስጥ መጥተዋል።

ወቅቱ ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎችን ያስተናገደችበት ቢሆንም ከዳያስፖራ ኢንቨስትመንት አንፃር የተመዘገበው አፈጻጸም ስኬታማ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳያስፖራው ባለፉት ሁለት ወራት ከአምስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስረዳትና የፐብሊክ ዲፕሎማሲን በማጠናከር ረገድም ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያወሱት።

በግጭቱ የተጎዱ አካባቢዎች ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻርም ዳያስፖራው እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ እንደሆነም ተናግረዋል።

በመንግሥትና ህወሓት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎም ዳያስፖራው ግንዛቤ እንዲኖረውና የተጠናከረ ሥራ እንዲሰራ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የሰላም ስምምነት የአገርን ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል በመሆኑ ዳያስፖራው ለስምምነቱ ተግባራዊነት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

''ዳያስፖራው የሚያደርገው ተሳትፎ መነሻውም መድረሻውም የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው'' ያሉት ዶክተር መሐመድ የአገር ብሔራዊ ጥቅም የሚከበረው ደግሞ ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ብለዋል።

ዳያስፖራው በፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ በኢንቨስትመንትና በዕውቀት ሽግግር የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ በማስቀጠል በኢትዮጵያ ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ የበኩሉን እንዲወጣ ዋና ዳይሬክተሩ  ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም