የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አሰራር መዘርጋት አለባቸው - የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

180

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ሕዳር 24 ቀን 2015 በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሥራ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታና ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተቋማቱን አቅም የሚያጎለብቱ የለውጥ ስራዎችን እያከናወንኩኝ ነው ብሏል።

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ የስራ ፈጣሪዎች ሳምንትን ምክንያት በማድረግ "ሚሊየን ፈተናዎች፤ ሚሊየን ዕድሎች" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡

ውይይቱም በዋናነት በአገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲሁም በዲጂታል ዘርፍ  ላይ የሥራ ፈጠራ ሥራዎችን ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን እንደገለጹት፤ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ሥራ ፈጠራን የሚያበረታቱ አሰራሮች ሊዘረጉ ይገባል።

ለዚህም ተቋማት አሰራራቸውን ማዘመን እንዲሁም ሕግና ደንቦችን ማሻሻል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የፐብሊክ ኢንተርፕርነርሽፕ አስተሳሰብ ባህል እንዲጎለብት የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በግልና በመንግሥት ዘርፎች መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የሥራ ዕድል ፈጠራን ማጎልበት እንደሚገባ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያሳሰቡት።

የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ በመንግሥት ተቋማት ያሉ አሰራሮች ሥራ ፈጣሪነትን ከማበረታታት አኳያ ክፍተት እንዳሉባቸው ጠቁመዋል፡፡

የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሥራ ሁኔታ ለአዳዲስ ሃሳቦችና ሥራ ፈጠራ ምቹ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የተቋማት ልማት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ንጉሴ፤ ኢትዮጵያ አሁን በደረሰችበት ዕድገት ደረጃና የቀጣይ ትልሞችን በሚመጥን መልኩ በመንግሥት ተቋማት የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህን ለማገዝ ደግሞ የፖሊሲ ማሻሻያ እየተዘጋጀ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህም ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲያሻሽሉ ከማድረጉም በላይ በአገልጋይነት መንፈስ የተላበሰ ሠራተኛ እንዲኖር ያግዛል ብለዋል።

ዓለም አቀፉ የሥራ ፈጣሪዎች ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ 15ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለዘጠነኛ ጊዜ ከትናንት በስቲያ አንስቶ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም