ጉባኤው አገራት ኢንተርኔት ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሆን በጋራ ለመስራት የተስማሙበት ነው - የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር

158

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ሕዳር 24 ቀን 2015 17ኛው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት አስተዳደር ጉባዔ  አገራት ኢንተርኔት ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሆን አገራት በጋራ ለመስራት የተስማሙበት መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ።

ከሕዳር 19 ቀን 2015 ዓ.ም አንስቶ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው ጉባኤ ተጠናቋል።

ጉባዔው በበይነ-መረብ አስተዳደር፣ በኢንተርኔት ተደራሽነት፣ በመሰረተ-ልማት፣ በሳይበር ደኅንነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንደገለጹት የጉባኤው ተሳታፊዎች የዓለም የትስስር መድረክና ትልቅ ሃብት የሆነው ኢንተርኔት ደኅንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ እንዲሆን አገራት በጋራ ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ የደረሱበት ነው ብለዋል።

የሳይበር ደህንነት፣ የፖሊሲ ጉዳይ፣ በመመሪያና በቁጥጥሮች ላይ ያሉ አሰራሮች  ተግባራዊ ሲደረጉ በሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ውይይት መደረጉንም አንስተዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ልምዱን አጋርቷል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በበይነ-መረብ አማካኝነት እንዲያከናውኑ ለማስቻል የ2025 የዲጂታል ስትራቴጂ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሰረታዊ በሆኑ የቴክኖሎጂ ባለቤትነትና የሳይበር ደኅንነት ማስጠበቅ ላይ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው አቶ ሰለሞን የገለጹት።

ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ተቋምን በሰው ኃይል፣ በዘመናዊ አሰራርና በአገር በቀል ቴክኖሎጂ እየገነባች ነው ብለዋል።

በጉባዔው ኢትዮጵያ የዘርፉን ተሞክሮዋን ከማጋራት ባለፈ ራሷን በሚገባ ማስተዋወቋን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም