የሶማሌ ክልል መንግሥት ክልላዊ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ አቋቋመ

204

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ሕዳር 24/2015 የሶማሌ ክልል መንግሥት ክልላዊ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ ማቋቋሙን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ ዛሬ ለኢዜአ በላከው መግለጫ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ አምስት አባላት ያለው ክልላዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ ዛሬ ማቋቋማቸውን አስታውቋል።

ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ክልላዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴውን ያቋቋሙት በክልሉ ሙስናን በመከላከልና በመቆጣጠር ለማስወገድ እንደሆነ  አመልክቷል።

ኮሚቴው አምስት አባላት ያሉት ሲሆን ዋና ተግባርና ኃላፊነቱ በክልሉ የሙስና ተግባራት ላይ ክትትልና ምርመራ በማድረግ በሙስና ተግባራት የተሳተፉ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ እንደሆነ ተነግሯል።

የኮሚቴው ሰብሳቢ የክልሉ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሃጂ  ሲሆኑ፤ የክልሉ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አብዲወሊ ጃማዕ፣ የክልሉ የኦዲት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ዩሱፍ፣ የክልሉ የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ  አቶ ጣይብ አህመድ እና  የክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ኢፍራህ መሀሙድ አባላት መሆናቸው በመግለጫው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም