የንግዱ ማኅበረሰብ ጤናው የተጠበቀና ጥራት ያለው ምርት የማቅረብ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

226

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ሕዳር 24 ቀን 2015  የንግዱ ማኅበረሰብ ጤናው የተጠበቀና ጥራት ያለው ምርት የማቅረብ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አሳሰበ።

በኦሮሚያ እስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት "ጠንካራ የሓላል ቁጥጥር ሥርዓት ለተሻለ ጤና እና ኢኮኖሚ ልማት" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ሲምፖዚየም ዛሬ ተካሄዷል።

ሲምፖዚየሙ በዋናነት ኢስላማዊ ሕግን መሰረት ባደረገ መልኩ በተለይ ለአረብ አገራት የሚቀርብ የሥጋ ምርት ጥራት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ እንዳሉት፤ጤናው የተጠበቀ ምርት ለሕብረተሰቡ ማቅረብ የሁሉም ሃይማኖቶች መርህ ነው።

ጤናማና ጥራታቸው የተጠበቁ ምርቶች ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት ፋይዳ የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

ከዚህ አኳያ የንግዱ ማኅበረሰብ ጤናው የተጠበቀና ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሀሚድ ጀማል በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ200 ቶን በላይ የሥጋ ምርት ለዓለም  ገበያ የማቅረብ አቅም እንዳላት ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በምርት ጥራት ላይ ባሉ ክፍተቶች እና ምርቱን በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅ ባለመቻሉ እስካሁን ወደ ውጭ የሚላከው የሥጋ ምርት ከ22 ሺህ ቶን እንደማይበልጥ ጠቁመዋል።

በመሆኑም በዘርፉ ያሉ ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመሥራት ኢትዮጵያ በሥጋ ምርት ያላትን አቅም እንድትጠቀም መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

ሲምፖዚየሙ ላይ የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ማህበራት ተሳትፈዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም