የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ የሚያስችለው ተቋማዊ አሰራሮችን የማጠናከር ስራ እያከናወነ ይገኛል

597

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ሕዳር 24 ቀን 2015 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ የሚያስችለው ተቋማዊ አቅም የማጠናከር ስራ እያከናወነ መሆን አስታወቀ።

ለምክር ቤቱ አባላት ባለፉት አራት ቀናት በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ዛሬ ተጠናቋል።

ሥልጠናው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን አቅም ለማጎልበት ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተለያዩ ችግሮች በተፈተነችበት ባለፉት ዓመታት ምክር ቤቱ ችግሮች ሳያቆሙት የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ሲሰራ ቆይቷል፤ከዚህም በተጓዳኝ ጠንካራ ምክር ቤት ለመፍጠር የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በቀጣይም ምክር ቤት ያሉ ተቋማዊ አሰራሮችን በማጠናከር ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር  አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ ስልጠናው የምክር ቤቱ አባላት ተጨማሪ አቅም እንዲያጎለብቱ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የምክር ቤቱን የማስፈጸም አቅም በማጎልበት ጠንካራ ምክር ቤት ለመፍጠር የሚደረገውን  ጥረት ያግዛል ብለዋል።

ሰልጣኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ስልጠናው አቅምን በማጎልበቱ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።