የአፍሪካ መንግሥታት ወጣቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጭ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሥራት አለባቸው

164

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 24/2015 የአፍሪካ መንግሥታት ወጣቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጭ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ሊሰሩ እንደሚገባ አፍሪካውያን ወጣቶች ተናገሩ።

በአፍሪካ 12 ነጥብ 7 በመቶ ወጣቶች ሥራ-አጥ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የአፍሪካ መንግሥታት  የሥራ-አጥ ቁጥርን ለመቀነስ በዲጂታል ኢንዱስትሪው ያለውን ትልቅ አቅም አሟጦ የመጠቀም ሥራ ማከናወን እንዳለባቸው ተገልጿል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የ17ኛው ዓለም አቀፍ የበይነ-መረብ አስተዳደር ጉባዔ ተሳታፊ ወጣቶች የዲጂታል ኢንዱስትሪው የሥራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ አቅም እንዳለው አንስተዋል።

ከዴሞክራቲክ ኮንጎ የመጣው ወጣት አታናሴ ሃህዚሬ በምጣኔ ሃብት ያደጉ አገሮች ኢንተርኔትን በመጠቀም ለወጣቶቻቸው አማራጭ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ያደረጉበትን ልምድ የአፍሪካ መንግሥታትም ሊተገብሩት ይገባል ብሏል።

በተለይም የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ተግባር ለመቀየር በገንዘብ መደገፍ የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋት እንደሚገባ ተናግሯል።

ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ሰላማዊት ገብረመስቀል የዲጂታል ኢንዱስትሪው አፍሪካውያን ወጣቶች ከዓለም ወጣቶች ጋር ተወዳዳሪ ሊሆኑበት የሚችሉትን ዕድል ይዞ መምጣቱን ትናገራለች።

ከሩዋንዳ የመጣው ተሳታፊ ወጣት ኤሪክ ሩኬቤሻ በበኩሉ፤ የዲጂታል ዘመን ለወጣቶች ይዟቸው የመጣውን በርካታ አማራጮች ለመጠቀም መንግሥታት ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አስገንዝቧል።

የዓለምን ምጣኔ ሃብት፣ ፖለቲካና፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴ እየተቆጣጠረ የሚገኘው የዲጂታል ዘመን ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።

በፈረንሳይ ሊሌ(Lille) ዩኒቨርሲቲ በዓለም አቀፍ ኤሌክትሮኒክስ ቢዝነስ ላይ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር መሃመድ ሃሰን በአፍሪካ የዲጂታል ምጣኔ ሃብትን በመገንባት ሂደት በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንደሚቻል አመላክተዋል።

አፍሪካ ካላት ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ 60 በመቶውን የሚይዘው ወጣቱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም