በጎፍቃደኞች ማህበረሰቡን ከማገልገል ጎን ለጎን የሌሎችን ባህሎች ሊማሩ ይገባል-ዶክተር ፍሬው ተገኝ

93

ባህርዳር (ኢዜአ) ህዳር 24/2015 በጎፍቃደኞች በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ማህበረሰቡን ከማገልገል ጎን ለጎን የሌሎችን ባህል ሊማሩ እንደሚገባ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ አስገነዘቡ።

የሰላም ሚኒስቴር ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለ5ኛ ዙር በበጎፍቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 200 ወጣቶች ዛሬ አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ  ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ  ነገዎ፣ የሰላም ሚኒስትር ተወካይ ዶክተር አወቀ አጥናፉና ሌሎች የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲው ለአንድ ወር በበጎፍቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥ ስልጠናቸውን ሲከታተሉ የቆዩ መሆናቸው ተገልጿል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በወቅቱ ባስተላለፉት  መልእክት በጎ ፈቃደኛ ተመራቂ ወጣቶች በሚመደቡበት አካባቢ እውቀታቸውንና ጉልበታቸውን ያለስስት በመለገስ ህብረተሰቡን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ።

"ኢትዮጵያ የብዘሃ ባህልና እሴት ሙዝየም በመሆኗ በበጎፍቃደኝነት ህብረተሰቡን ማገልገል የሌላውን ባህል ለማወቅ እድል የሰጠ ነው" ብለዋል።

ተመራቂ በጎ ፍቃደኞች በሚሰማሩባቸው አካባቢዎች ህብረተሰቡን ከማገልገል ጎን ለጎን የራሳቸውን ባህል በማስተማር፣ የሌሎችን ባህልና እሴት ለመማር ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ዩኒቨርሲቲው በጎፈቃደኛ ወጣቶች ማወቅ የሚጠበቅባቸውን እውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ ጥረት ማድረጉን ገልፀዋል።

"የኢትዮጵያን ህዝብ በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ዕድል ማግኘት በራሱ እድለኝነት ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ ወጣቶቹ እድሉን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ተመራቂ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውንና ቀና አስተሳሰባቸውን በመጠቀም በሚመደቡበት አካባቢ በትጋት በማገልገል ሀገራቸውና ህዝባቸውን መጥቀም እንደሚጠበቅባቸው ጨምረው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም