በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ፆታዊ ጥቃቶችን ለማስቀረት በትኩረት ይሰራል-የጋምቤላ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

342

ጋምቤላ (ኢዜአ) ሕዳር 23/2015 በጋምቤላ ክልል በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ፆታዊ ጥቃቶችን ለማስቀረት በትኩረት ይሰራል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

‘‘ሴቶችን አከብራለሁ፣ ጥቃታቸውንም እከላከላለሁ’’ በሚል መሪ ሃሰብ ዓለም አቀፉ የነጭ ሪቫን ቀን በክልል ደረጃ በጋምቤላ ከተማ በፓናል ውይይት ተከብሯል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችንና ፆታዊ ጥቃቶችን በማስቀረት ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የሴቶችን ሁለንተናዊ መብት ለማረጋገጥ በርካታ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ቢኖሩም አሁንም ድረስ በሴቶች ላይ የተለያዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ፆታዊ ጥቃቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም የክልሉ መንግስት የሀገር ሽማግሌሎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን የፍትህ አካላትንና ሌሎች አደረጃጀቶችን በመጠቀም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቀረት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ክርምስ ሌሮ በበኩላቸው በክልሉ ያለ እድሜ ጋብቻና ፆታዊ ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ በሚፈጸም ያለ አድሜ ጋብቻ ሴቶች ልጅነታቸውን ሳይጨርሱ የልጅ እናት በመሆን ትምህርታቸውን በማቋረጥ ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተዳረጉ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመሆኑም ቢሮው ችግሩን ለማስቆም ለሚደረገው ጥረት መሳካት ከወላጆች ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ትሁት ቶቤል በሰጡት አስተያየት የአስገድዶ መድፈርን ጭምሮ ሌሎች በሴቶች ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ አስተማሪ የህግ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ያሉት ውስንነቶች ሊታረሙ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አኳይ አቡቲ የአስገድዶ መድፈረም ሆነ ሌሎች በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የማስቀረቱ ስራ በፍትህ ተቋማት ብቻ ውጤታማ አይሆንም ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለማስቀረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅትና ተባብሮ መስራትን የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን አቶ አኳይ ገልጸዋል።  

የዓለም የነጭ ሪቫን ቀን  በዓለም ለ31ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ እየተከበረ ነው።