የኦሮሚያ ክልል ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሰበሰበው ገቢ በአርአያነት የሚጠቀስ ነው-ዶክተር አረጋዊ በርሄ

179

አዳማ (ኢዜአ) ህዳር 23/2015 የኦሮሚያ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሰበሰበው ገቢ በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አረጋዊ በርሄ አስታወቁ።

በህዳሴው ግድብ ግንባታ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንዳሉት የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በኦሮሚያ ክልል በቆየበት አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 1 ቢሊዮን 48 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል።

ባለፈው አንድ ዓመት የህዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ በዞኖችና ከተሞች አቀባበል በማድረግ የተሰበሰበው ገቢ አርአያ ሊሆን የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።

"የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስና የኢትዮጵያ ህዝብ ምኞትና ህልም እውን እንዲሆን ሀገሪቷ ዘርፈ ብዙ ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት ጭምር ግንባታው ለአፍታም ሳይቆም መቀጠሉ የጥንካሬያችን ማሳያ ነው" ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል የህዳሴ ግድብ የገቢ ማሰባሰቢያ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ቆንጂት በቀለ በበኩላቸው በክልሉ ባለፈው አንድ ዓመት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ 600 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የታቀደ ቢሆንም 1 ቢሊዮን 48 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

"የአባይ ወንዝ ጥቅም ሳይሰጥ መቆየቱ ህዝቡ ውስጥ ያለው ቁጭትና ለግድቡ ውጤታማነት የማይከፍለው ዋጋ እንደሌለ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ሀገር ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ትልቅ ግምት የሚሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በፓናል ውይይቱ የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በህዳሴው ግድብ ግንባታና ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በአረንጓዴ አሻራ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን የዳሰሱና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያመላከቱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም