የአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የ''ድሽታ-ግና'' በዓል በጂንካ ከተማ እየተከበረ ነው

312

ጂንካ(ኢዜአ) ህዳር 23 ቀን 2015  ሰላምን፣ ፍቅርን እና አንድነትን የሚሰብከው የአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ''ድሽታ-ግና'' በዓል በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

ከህዳር ወር አጋማሽ እስከ ታህሳስ ወር መግቢያ የሚከበር ባህላዊ ስርአት የሆነው "ድሽታ ግና" በዓል  የአሪ ብሔረሰብ ደማቅ አሻራ ነው።

የደቡብ ኦሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህልና ቅርስ ጥናት ጥበቃ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዳኜ ገብሬ በዓሉ ለልማት፣ ለሰላምና ለአብሮነት ጉልህ ሚና የሚጫወት  ባህላዊ እሴት እንደሆነ ተናግረዋል።

"ድሽታ ግና" በዋናነት በአባቶች የእህል ቀመሳ ስርዓት የሚፈፀምበት እና አዲሱ አመት የሰላም፣ የፍቅር እና የመተሳሰብ እንዲሆን ቡራኬ የሚሰጡበት፤ አሮጌውን ዓመት በመሰናበት አዲሱን ለመቀበል በጉጉት ጠብቀው የሚያከብሩት የዘመን መለወጫ በዓል እንደሆነም ገልጸዋል።

"ድሽታ ግና" በውስጡ መተሳሰብን፣ መረዳዳትን፣ ይቅርታና ዕርቀ ሰላምን የመሳሰሉ ሰዋዊ ዕሳቤዎች የያዘ ባህላዊ ክዋኔ በመሆኑ ለማህበራዊ ዕሴት መጠናከር የላቀ ፋይዳ እንዳለውም አስረድተዋል።

በዓሉ አገር  ሰላም እንዲሆን፣ በሽታ እንዲጠፋ፣ የተቀያየሙ እንዲታረቁና ህዝቡ አዲሱን አመት ቂምና ቁርሾ ሳያሳድር በይቅርታ ለመቀበል የሚከወን ባህላዊ ስርዓት መሆኑን አመላክተዋል።

ከበዓሉ ዕሴቶች ውስጥ ምስጋና ማቅረብ፣ እርስ በርስ መረዳዳት፣ ፍቅር መግለጽ፣ ዕርቀ ሰላም ማውረድ፣ አብሮነትን ማጠናከር እና ጽዳትና ውበትን መጠበቅ የሚያካትቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዓሉ ያለፈውን ዘመን የተፈጠሩ ቁርሾዎችና ቂም በማስወገድ አዲሱን ዘመን በሰላምና በተስፋ ለመቀበል የሚደረግ በመሆኑ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል።

የበዓሉ መከበርና ተጠብቆ መቆየት ለሰላምና ልማት መጠናከር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ለአብነትም በዓሉን ማስተዋወቅ አንዱ ተግባር መሆኑን አንስተዋል።

የድሽታ ግና በዓል ጂንካ ከተማን ጨምሮ በአሪ ወረዳዎች ማለትም በደቡብ አሪ፣ በሰሜን አሪ፣ በዎባ አሪ  እና በባካ ዳውላ አሪ ወረዳዎች ከህዳር ወር አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ ባህላዊ ስርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።

የበዓሉ ማጠቃለያ መርሃ ግብር የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ታህሳስ 1 ቀን 2015 ዓም እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም