በዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ቴክኒካል ረዳቶች ስም የተሰራጨውን አቋም ማህበራችን አያውቀውም -የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር

375

አዲስ አበባ ህዳር 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ቴክኒካል ረዳቶች ስም የተሰራጨውን አቋም ማህበራችን አያውቀውም ሲል የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ለኢዜአ በላከው መግለጫ ማህበሩ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምሀርት ድረስ መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎችን በማደራጀት በአምስት ዓላማዎች እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጿል።

ከአምስቱ ዓላማዎች መካከል አንዱ የመምህራን መብትና ጥቅም ማስከበር ነው ያለው መግለጫው በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርሲቲ መምራን ያነሱትን ጥያቄዎች ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሚመለክታቸው የፌዴራል መንግስት አካላት እያቀረበ ለመፍትሄው እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል።

አንዳንድ ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ ማግኘት የሚገባቸው መሆኑን ማህበሩ ቢያምንም አንዳንዶቹ ደግሞ ጊዜ የሚፈልጉ መሆናቸው ሊታወቅ እንደሚገባም አስታውቋል።

የመምህራን ማህበር የትግል ስልት መርህን መሰረት በማድረግ ለሌሎች አርዓያና ትምህርት ሰጪ በሆነ መልኩ መሆን እንዳለበትም የማህበሩ መግለጫ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እያለ "የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራንና ቴክኒካል ረዳቶች የአቋም መግለጫ” በሚል ርዕስ “ከህዳር 26/2015 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ የሥራ ማቆም አድማ እናደርጋለን" በሚል ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨውን መረጃ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር የማያውቀው ነው በማለት አስታውቋል።

እውቅና ያለው የማህበሩ መዋቅር ስምም “የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን ማህበር" መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው መምህራንም ማህበራችሁ ጉዳዩን በጥብቅ ይዞ እየሰራ መሆኑን አውቃችሁ የተለመደውን የማስተማር የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ሙያዊ ኃላፊነታችሁን እንድትቀጥሉ ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም