በኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ የማኅበረሰብ የጤና ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል-ዶክተር ሊያ ታደሰ

773

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 22/2015 በኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ የማኅበረሰብ የጤና ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተናገሩ፡፡

34ኛው ዓለም አቀፍ ኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን "ፍትሃዊና ተደራሽ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ አገልግሎት" በሚል መሪ ሃሳብ ታስቦ ውሏል፡፡

በእለቱ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰን ጨምሮ የክልልና የከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች፣ በዘርፉ የሚሰሩ ማህበራት ተወካዩች፣ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ አሁንም የማኅበረሰብ ጤና ችግር ሆኖ ቀጥሏል።

በመሆኑም ለኤች አይ ቪ ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች የምርመራና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል።

ኤች አይ ቪ/ኤድስ ዓለምን በከፍተኛ ሁኔታ የፈተነ ሲሆን እስካሁን ከ40 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለህልፈት ሲዳርግ 38 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ላይ 617 ሺህ 921 ዜጎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 62 በመቶው የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. 8  ሚሊዮን ሰዎች ላይ በተደረገ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ምርመራ 35 ሺህ የሚሆኑት ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደተገኘ ተናግረዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴር ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ሥርጭቱን ለመግታት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸው፤ ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡንም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የበሽታውን የሥርጭት መጠን ከ1 ነጥብ 5 ወደ 0 ነጥብ 93 ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሥርጭት መጠኑ መቀነስ ቢታይበትም የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ሚኒስቴሩ በቀጣይ ቫይረሱ የማኅበረሰብ የጤና ችግር እንዳይሆን የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በተለይ ቫይረሱ ያለባቸውን ሰዎች በምርመራ የመለየት፣ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ የማድረግ እና የቅድመ-መከላከል ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡

ፍትሃዊ  የኤች አይ ቪ ሕክምና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግም ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት ይሰራበታል ነው ያሉት፡፡

ቀኑ በዓለም ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ታስቦ ውሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም