በአዲስ አበባ 24ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ ሊካሔድ ነው

127

ህዳር 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) 24ኛው የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ሕብረት ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ብሔራዊ ኢንተርፖል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ፀጋዬ ኃይሌ በሰጡት መግለጫ ከፊታችን እሁድ ማለትም ከህዳር 25 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም የሚካሄደውን ጉባዔ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

በስብሰባው በፀረ ሽብርተኝነት እና በሌሎች የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ የሕብረቱን መሪነት በዕጩነት የምትረከብ ሲሆን በዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ተረክበው ለአንድ ዓመት ይመራሉ ነው ያሉት።

ለቀጣናው ትልቅ ፋይዳ ያለው ስብሰባ መሆኑን ገልፀው፣ የእስከ አሁን ስራዎች የስራ አፈፃፀም ግምገማ እና ተሞክሮ ልውውጥ ይደረጋል ብለዋል።

ወጥ የፖሊስ አሰራር ለመመስረት ስምምነት ላይ እንደሚደርሱም ይጠበቃል ነው ያሉት።

በሽብር ወንጀል፣ የሰዎችና ጦር መሳሪያ፣ የአደንዛዥ ዕፅና የእንስሳት ዘረፋ ስራዎችም ይገመገማሉ ነው ያሉት።

ስብስባውም በአፍሪካ ሕብረትና በስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ ገልፀዋል።

በስብሰባው የኢንተርፖል ኃላፊዎች፣ አታሼዎች፣ የየአገራቱ ፖሊስ ተቋማት ኃላፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።

ከዚህ ቀደም 23ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ሕብረት ዓመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኪንሻሳ መካሄዱ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያም ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው የምታስተናግደው።

ተቀማጭነቱን በናይሮቢ ኬኒያ ያደረገው ሕብረቱ በምስራቅ አፍሪካ አገራት የሕግ አስከባሪ ተቋማትን ትብብር ለማጠናከር፣ የመረጃ ልውውጥን ለማጎልበት፣ የጋራ ስትራቲጂ ለመንደፍ የሚሰራ ሲሆን በቀጣናው ሰላም ለማስፈን በተለይም ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመመከት ግብ ይዞ በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 1998 በኡጋንዳ ካምፓላ ነበር የተቋቋመው።

14 አገራትን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን አባላቱም ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሲሸልስ፣ ሩዋንዳ፣ ኤርትራ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኮሞሮስና ቡሩንዲ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም